Version classiqueVersion mobile

Bulletin de la Maison des études éthiopiennes | Novembre 1993. N°3

 | 
Jacques Bureau

Conseils sur le voyage d'Europe

ስለ አውሮጳ መንገድ የምክር ቃል

Texte intégral

1በልዑል ኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት ታተመ መጋቢት ፳ ቀን ፲፱፻፲፯ ዓመተ ምሕረት፡፡
ሁለተኛ በብርሃንና ሰላም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ማተሚያ ቤት ታተመ፡፡
ሚያዝያ ፮ ቀን ፲፱፻፵፰ ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ፡፡

ስለ አውሮጳ መንገድ የምክር ቃል፡፡

2ለትምህርትም ቢሆን ለንግድም ቢሆን ወይም ከመንግሥት ተልኮም ቢሆን ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገር የሚሔድ ሰው ሁሉ ይህን የምክር ቃል ማንበብ ይገባዋል፡፡

ስለ ይለፍ ወረቀት ፓስፖርት፡፡

3፩ ወደ ውጭ አገር ለመሔድ የሚፈልግ የኢትዮጵያ ሰው ሁሉ ለመንገዱ መነሣት 15 ቀን ሲቀረው የይለፍ ወረቀቱን ነገር መጨረስ ያስፈልገዋል፡፡ ይህንንም የይለፍ ወረቀት መቀበል የሚያስፈልገው መጀመሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡

4፪ የይለፍ ወረቀቱን ከኢትዮጵያ መንግሥት ከተቀበለ በኋላ የሚሔድበትን አገር አስታውቆ ወደ ሌጋሲዎን ሔዶ የቆንስሉን ፊርማ በይለፍ ወረቀቱ ላይ ማስፈረም ነው፡፡ በየመንግሥቱም የሚሄድ የሆነ እንደሆነ በአዲስ አበባ ከሚኖሩት ቆንስሎች ሁሉ ማስፈረም ያስፈልጋል፡፡

ስለ መርከብ መገኘት፡፡

5፫ መርከብ ጅቡቲ የሚገኝበትን ጊዜ ከ15 ቀን በፊት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህንኑም ለማወቅ በጅቡቲ ወዳጅና ዘመድ ያለው ሰው በጽሕፈት ወይም በቴሌግራም መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በጅቡቲ ወዳጅና ዘመድ የሌለው ግን በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ቆንስል ቤት ለመጠየቅ ይችላል፡፡

6፬ መርከቡ ጅቡቲ የሚገኝበት ጊዜው ከታወቀ በኋላ ስለ ቦታው እንደ አቅሙ በመጀመሪያው ወይም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ማዕርግ ቦታ መገኘቱን ከኩምፓንያው ጠይቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ቦታው መገኘቱ እርግጡ ከታወቀ በኋላ መርከቡ ከጅቡቲ ከሚነሣበት ጊዜ ከሁለት ቀን በፊት ጅቡቲ መድረስ ያስፈልጋል፡፡

በምድር ባቡር ስለ መሳፈር፡፡

7፭ በመንግሥት ፈቃድ በእኩሌታ ዋጋ በባቡር የሚሳፈር ሰው ካንድ ቀን በፊት የፈቃድ ወረቀቱን መቀበል ያስፈልገዋል፡፡

8፮ ባቡሩ ለመነሣት አንድ ሰዓት ሲቀረው በባቡር ማቆሚያ ደርሶ የባቡሩን መግቢያ ወረቀት ለመቀበል ገንዘቡን መክፈል ነው፡፡ ብዙ ዕቃ ያለው ሰው ግን ከ2 ሰዓት አስቀድሞ በባቡር መቆሚያ ደርሶ ዕቃውን ማሳፈር ያስፈልገዋል፡፡ ዕቃውንም ሲያሳፍር ከኩምፓኒያው የደረሰኝ መቀበል ያስፈልገዋል፡፡ ነገር ግን ይህ የሚቀበለው የደረሰኝ የጠፋ እንደሆነ ኩምፓኒያው አላፊነት የለበትምና ተጠንቅቆ መጠበቅ ነው፡፡

9፯ በባቡር የሚሳፈር ሰው የመቀመጫውን ስፍራ ሌሎች ሰዎች ሳይዙበት በቶሎ ገብቶ ባርኔጣውን ወይም የብርድ ልብሱን ዌም መጽሐፉን በመቀመጫው ላይ ማኖር ያስፈልገዋል፡፡ ይህን ሳያደርግ ቀረ እንደ ሆነ ግን ወደ ውጭ በወጣ ጊዜ ሌላ ሰው ገብቶ ስፍራውን ሊይዝበት ይችላል፡፡

10፰ በባቡር ውስጥ በሳጥን ያልገባ ትንንሽ ዕቃ የያዘ ሰው በጣም ተጠንቅቆ መጠበቅ ያስፈልገዋል፡፡ ሻንጣውንም ደኅና አድርጎ መቆለፍ ነው፡፡

11፱ ባቡር በየጣቢያው በሚቆምበት ጊዜ የሚቆመው ስንት ደቂቃ መሆኑን ሳያውቁ ወደ ምድር መውረድ አይገባም፡፡ የሚቆምበት ጊዜ ስንት ደቂቃ እንደ ሆነ ሳያውቁ ወደ ምድር የወረዱ እንደ ሆነ ባቡሩ በድንገት በተነሣ ጊዜ ሮጦ ለመግባት ብዙ ችግር ይሆናል፡፡

12፲ በየጣቢያው ባቡሩ በቆመ ጊዜ በባቡሩ ውስጥ ባለው ሠገራ ቤት ገብቶ ሽንት መሽናት ሌላም ጉዳይ ማድረግ አይገባም፡፡ ይህን የመሰለውን ጉዳይ ሁሉ መፈጸም ባቡሩ በሚሔድበት ጊዜ ነው፡፡

13፲፩ ባቡሩ በሚሔድበት ጊዜ ሁሉ በመስኮት አንገትን ወይም እጅን ብቅ ማድረግ ክልክል ነው፡፡ ብቅ ያደረገ እንደሆነ ግን ከባቡሩ ፍጥነት የተነሣ ከእንጨት ጋራ ወይም ከገደል ጋራ አጣብቆ ይቆርጠዋል፡፡

14፲፪ ከባቡር ለመውረድ ጊዜው በደረሰ ጊዜ ዕቃን ሁሉ በጥንቃቄ ማውረድ ያስፈልጋል፡፡ ዕቃውም ከወረደ በኋላ የሚሸከሙት ኩሌዎች ተሸካሚዎች ኑሜሮአቸው በክንዳቸው ወይም በቆባቸው ይጻፋልና በጥንቃቄ አይቶ ኑሜሮውን በቶሎ መጻፍ ነው፡፡

15፲፫ ዕቃው ሁሉ ከባቡር ከወረደ በኋላ የጉምሩኩን ጣጣ ጨርሶ ወደ ሆቴል ዌም ወደ ዘመድ ቤት ዕቃን አሸክሞ መሔድ ነው፡፡

16፲፬ ጅቡቲ በደረሱ በማግሥቱ ወደ ዘበኛ አለቃ ጽሕፈት ቤት ሔዶ የይለፍ ወረቀቱን አሳይቶ በላዩ ማስፈረም ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ መርከቡ ኩምፓኒያ ሔዶ ገንዘቡን ከፍሎ የመርከቡን መግቢያ ወረቀት (ቢዬ) መቀበል ያስፈልጋል፡፡

ወደ መርከብ ስለ መግባት፡፡

17፲፭ መርከቡ ጅቡቲ ከገባ በኋላ ብዙ ዕቃ ያለው ሰው በፍጥነት ጀልባ ተከራይቶ አስቀድሞ ዕቃውን አግብቶ የደረሰኝ መቀበል ያስፈልገዋል፡፡ የልብስ ሻንጣ ብቻ የያዘ ሰው ግን እርሱ በሚገባበት ጊዜ ይዞ ለመግባት ይችላል፡፡

18፲፮ መርከቡ ለመጓዝ አንድ ሰዓት ሲቀረው ወደ መርከብ መግባትና ስፍራን ተቀብሎ መቆየት ያስፈልጋል፡፡

19፲፯ ወደ መርከብ በመግባት ጊዜ በመጀመሪያ የመርከቡን መግቢያ ወረቀትና የይለፍ ወረቀቱን ለመርከቡ ሹሞች ማሳየት ያስፈልጋል፡፡

20፲፰ በመርከብ ውስጥ የመኝታ ስፍራ ከመቀበል በኋላ በፍጥነት የሠገራ ቤቱንና የመታጠቢያ ቤቱን ቀጥሎም የምግቡን ቤትና የጽሕፈት ቤቱን የጻሕፍት ማንበቢያ ቤቱን ማየትና ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

21፲፱ በመርከብ ውስጥ ለቁርስ ለምሳ ለሻይ ለራት የተወሰነውን ሰዓት ማወቅና በጊዜው ከሥፍራው መገኘት ይገባል፡፡ ሰዓቱ ካለፈ በኋላ ግን ምንም ለማግኘት አይቻልም፡፡

22፳ በመርከብ ውስጥ አልማዝና ወርቅ ሌላም ክቡር ዕቃ ያለው ሰው ሁሉ ተጠንቅቆ መጠበቅ ይገባዋል፡፡ ለመጠበቅ የማይችል የሆነ እንደ ሆነ ግን ለመርከቡ ሹም አስረክቦ የደረሰኝ መቀበል ነው፡፡ ክቡር ዕቃውን ተጠንቅቆ ሳይጠብቅ ወይም ለመርከቡ ሹም ሳያስረክብ ቀርቶ የጠፋበት እንደሆነ የመርከቡ ኩምፓኒያ አላፊነት የለበትም የሚል ደምብ አላቸውና በጣም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

23፳፩ በመርከብ ውስጥ ሰው ሁሉ በየስፍራው አርፎ መቀመጥ ነው እንጂ የሦስተኛው ማዕርግ ወደሁለተኛ የሁለተኛው ማዕርግ ወደ መጀመሪያው እንዳይተላለፍ ክልክል ነው፡፡ ነገር ግን ለብርቱ ጉዳይና ሰው ለመገናኘት አሽከር ከጌታው ትእዛዝ ለመቀበል ቢፈልግ ላንድ አፍታ መተላለፍ አይከለከልም፡፡

24፳፪ ወደ መርከብ የሚገባ ሰው ሁሉ አንዳንድ ምቹ ወምበር ይዞ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ወይም የመርከቡ ኩምፓኒያ ወምበር ያከራያልና መከራየት ነው፡፡ ለጊዜው ባለቤቱ ባይኖር እንኳ በሌላ ሰው ወምበር ላይ መቀመጥ ክልክል ነው፡፡

25፳፫ በመርከብ ውስጥ በመጀመሪያውና በሁለተኛው ማዕረግ የሚገባ ሰው በአራት ጊዜ ጥሩ ጥሩ ልብስ መልበስ ያስፈልገዋል፡፡

26፳፬ በመርከብ ውስጥ ባዳራሹ (ሳሎን) ወይም በመናፈሻው ስፍራ በትልልቆች ሰዎችና በወይዛዝርት ፊት ነጠላ ጫማ አድርጎና የሌሊት ልብስ ለብሶ መታየትና መሄድ ትልቅ ነውር ነው፡፡

27፳፭ በመርከብ ውስጥ የኤሌክትሪኩን መብራት ፀሓይ ከጠለቀች ጀምሮ ፀሓይ እስክትወጣ ባስፈለገ ጊዜ ማብራት አይከለከልም ፀሓይ ከወጣች በኋላግን የመብራቱን መኪና ማቆም ይገባል፡፡

28፳፮ በመርከብ ውስጥ ሙቀት በጸና ጊዜ ነፋስ የሚያመጣውን የኤሌክትሪክ መኪና ባስፈለገ ጊዜ መዘወር ነው፡፡ ባላስፈለገና ወደውጭ በመውጣት ጊዜ ግን መኪናውን አቁሞ መውጣት ይገባል፡፡

29፳፯ ወደሠገራ ቤት በመግባት ጊዜ መዝጊያውን ከወደ ውስጥ አጠንክሮ መዝጋት ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩንም ጨርሶ በመውጣት ጊዜ ባጠገብ በተሰቀለው ውኃ እድፉ እንዲወርድና ንጹሕ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ እድፉን በውኃ ንጹሕ ሳያደርጉ ከሠገራ ቤት መውጣት ትልቅ ነውር ነው፡፡ በኋላም መዝጊያውን ክፍቱን ትቶ መውጣት ነው እንጂ ዘግቶ መውጣት አይገባም፡፡

30፳፰ በመርከቡ ውስጥ በየመኝታው ቤት ደወል አለና የቸገረ ነገር የተገኘ እንደሆነ በጣት ጫን አድርጎ መደወል ነው የመርከቡ አገልጋይ ደወሉን ሰምቶ ያልመጣ እንደሆነ ሦስት ደቂቃ ያህል ቆይቶ መደወል ነው፡፡

31፳፱ በመርከብ ውስጥ ማታ ማታ ጫማን አውልቆ በመዝጊያው በስተውጭ ማስቀመጥ ነው፡፡ በማለዳ ጫማ ጠራጊ መጥቶ ጠርጎ ወልውሎ መልሶ በዚያው ስፍራ አስቀምጦት ይገኛል፡፡

32፴ በመርከብ ውስጥ ጧት ከ3 ሰዓት በኋላ ከመኝታ ቤት ወጥቶ በመናፈሻው ስፍራ ዌም በመጽሐፍ ማንበቢያው ስፍራ መቀመጥ ነው፡፡ በዚያ ጊዜ ቤት ጠራጊ ወደ መኝታ ቤት ገብቶ ስፍራውን ንጹሕ አድርጎ አልጋውን አንጥፎ ይወጣል ቤቱ ከተጠረገ በኋላ ቢያስፈልግ ተመልሶ ለመግባት ይሆናል፡፡

33፴፩ በመርከብ ውስጥ በየለቱ ወይም በሁለት በሁለት ቀን ልብስ መለወጥ ያስፈልጋል፡፡

34፴፪ በመርከብ ውስጥ በየለቱ ወይም በሁለት በሁለት ቀን ሁሉ አካልን መታጠብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚሁ የሚያስፈልገውን ሳሙና ፎጣ ሰፍነግ መያዝ ነው፡፡ ወደ መታጠቢያ ቤት በመግባት ጊዜ ከወደ ውስጥ መዝጊያውን አጠንክሮ መዝጋት ነው፡፡ ከ10 ደቂቃ የበለጠ በመታጠቢያ ቤት መቆየት አይገባም፡፡

35፴፫ በመርከብ ውስጥ የመርከቡ ሹም ሳይፈቅድ ምግብ ወደ ሚሰናዳበት ወጥ ወደሚቀቀልበት ስፍራ መግባት አይገባም ደግሞ አለፈቃድ መርከቡን የሚያስኬደውን መኪና ለማየት መግባት ክልክል ነው፡፡

36፴፬ መርከቡን የሚያስኬደውን መኪና ለማየት ፈቃድ ተቀብሎ በመግባት ጊዜ ብዙ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ መኪናው እርስ በርሱ የተቀረቀረበና የቴያዘ ስለሆነ ልብስ ጠልፎ የያዘ እንደሆነ የሞት አደጋ ያመጣል ስለዚህ ወደ መኪናው አለመቅረብ ያስፈልጋል፡፡

37፴፭ ወንዶች ወደ ሴቶች ሠገራ ቤትና መታጠቢያ ቤት እንዳይገቡ ክልክል ነውና ስፍራውን ተጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

38፴፮ ከመርከብ በመውረድ ጊዜ ለመርከብ አገልጋዮች እንደተቻለ ጥቂት ጥቂት ገንዘብ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

39፴፯ ከመርከብ በመውጣት ጊዜ በፍጥነት ዕቃን ማውጣት ይገባል፡፡ የጠፋ ዕቃም ቢኖር የደረሰኝ ወረቀት ካልጠፋ የመርከቡ ኩምፓኒያ አላፊ ይሆናልና የደረሰኙን ለመርከቡ ሹማ ማሳየት ነው፡፡

በመርከብም በባቡርም በሆቴልም በማናቸውም ስፍራ ቢሆን ለማድረግ የማይገባ

40፴፰ በማናቸውም ስፍራ ቢሆን ልብስን አፍንጫ ላይ ማድረግ ወይም ራስን መከናነብ አይገባም፡፡

41፴፱ ጧት ጧት ራስን ፊትን ሳይታጠቡ ወደ ውጭ መውጣት አይገባም ደግሞ በጥርስ ቡርሽና በሳሙና ጥርስን አፍን መታጠብ ነው፡፡ ደግሞ በጥፍር ውስጥ እድፍ እንዳይታይ በየጊዜው ማውጣት ያስፈልጋል፡፡

42፵ በትልልቅ ሰዎች ፊት ልቁንም በወይዛዝር ፊት ጥርስን መፋቅ ከጥፍር ውስጥ እድፍ ማውጣት አይገባም፡፡

43፵፩ ከትልልቅ ሰዎች ጋራ ልቁንም ከወይዛዝር ጋር ሲነጋገሩ እግርን አጣምሮ መቀመጥ መጨጊያ ተንተርሶ በጎድን መጋደም አይገባም፡፡

44፵፪ ትልልቅ ሰዎች ይልቁንም ወይዛዝሮች ለመጠየቅ በመጡ ጊዜ ከወምበር ተነሥቶ ቆሞ አክብሮ መቀበል ይገባል፡፡ ተቀምጦ እንግዳ መቀበል ግን ትልቅ ነውር ነው፡፡ ትልቅ እንግዳ በመጣ ጊዜ አክብሮ ተቀብሎ በብሩህ ገጽ በደስታ ማነጋገር ነው እንጂ ፊትን አጥቁሮ ተከፍቶ ማነጋገር አይገባም፡፡ ደግሞ ትልቅ እንግዳ ተቀምጦ ሳለ እርሱን ማነጋገር ትቶ ጋዜጣ ማንበብ ጽሕፈት መጻፍ አይገባም፡፡

45፵፫ ትልቅ እንግዳ በመጣ ጊዜ በንግግሩ መካከል ሰዓት አውጥቶ ማየት ለባለቤቱ አይገባውም፡፡ እንግዳ ተቀምጦ ሲነጋገር ሰዓት አውጥቶ ማየት ሒድልኝ ከማለት ይቆጠራል፡፡ ነገር ግን ወደ ሰው ቤት ሔዶ ጉዳዩን የሚነጋገር ሰው በንግግሩ መካከል ሰዓት አውጥቶ ቢያይ እርሱ ለመሔድ መቸኮሉን ያስረዳልና ነውር የለበትም፡፡

46፵፬ በመብልና ባካሔድ በመቀመጥም ጊዜ ወይዘቀዝርን መቅደም አይገባም፡፡ በስፍራውም ያለው ወምበር ለሁሉ የማይበቃ የሆነ እንደሆነ ወምበሩን ለወይዘቀዝር ለቆ መቆም ይገባል፡፡

47፵፭ ከትልልቆች ሰዎች ጋራ በመነጋገር ጊዜ ፊት ለፊት ሆኖ ዓይን ላይን እየተያዩ መነጋገር ነው እንጂ ፊትን አዙሮ ወይም በዓይን ሌላ ነገር እያ መነጋገር አይገባም፡፡

48፵፮ በቤተመንግሥትም ቢሆን በፋብሪካም ቢሆን የሚታይ ነገር ለማየት በመግባት ጊዜ ልብን አንቅቶ እንደዋዛ ዓይንን ጣል አድርጎ ማየት ነው እንጂ ከባላገር እንደ መጣ ሰው ዓይንን እያቅበዘበዙ ማየት አይገባም፡፡

49፵፯ በሰውም ፊት ቢሆን ለብቻም ቢሆን አክ ብሎ አክታ ወደ ምድር መትፋት አይገባምና በቀስታ አክ ብሎ በመሐርም መቀበል ነው፡፡ በመናፈጥም ጊዜ አፍንጫን በመሐርም አጥብቆ ዞ በቀስታ መናፈጥ ነው እንጂ ድምጡን አሰምቶ በኃይል መናፈጥና ወደ ምድር መጣል አይገባም፡፡

50፵፰ ቡን ወይም ሾርባ በመጠጣት ጊዜ ሙቀቱ ሲበርድ በቀስታ ሳብ አድርጎ መጠጣት ነው እንጂ ትንፋሽን አሰምቶ ፉት ማድረግ አይገባም፡፡

51፵፱ በምግብ ጊዜ ወጡን በትንሹ መውሰድ ነው እንጂ በብዙ መውሰድ አይገባም፡፡ ቢያስፈልግ ግን እንደገና መውሰድ አይከለከልም፡፡

52፶ በምግብ ጊዜ አፍን ገጥሞ በቀስታ ማላመጥ ነው እንጂ አፍን ከፍቶ መመገብና አፍን እያጮሁ ማላመጥ አይገባም፡፡

53፶፩ በምግብ ጊዜ ወይም በሌላ ጊዜ ብዙ መጠጥ መጠጣት ነውር ነው፡፡ የወይን ጠጅም በመጠጣት ጊዜ ውኃ እየደባለቁ መጠጣት ነው እንጂ ብቻውን መጠጣት ሰውነት ይጎዳል፡፡ አረቄ መጠጣት ለትልቅ ሰው በጭራሽ ቢቀርበት መልካም ነው፡፡ ለመተው የማይችል ሰው ግን አንድ መለኪያ ብቻ ይጠጣ እንጂ ከዚህ የበለጠ ቢጠጣ ነውር ይሆንበታል፡፡

54፶፪ በቤተ መንግሥት በሌላም በትልልቅ ስፍራ በቤተ ክርስቲያንም በትልልቅ ሰዎችም ፊት ቀስ ብሎ በእርጋታ መሄድ ነው እንጂ የጫማ ድምጥ እስቲሰማ እየረገጡ እየተገላመጡ መሄድ አይገባም፡፡

55፶፫ ከትልቅ ሰው ጋራ በመነጋገር ጊዜ በለዘብታና በቀስታ ቃል መነጋገር ነው እንጂ እየጮሁ መነጋገር አይገባም፡፡ በመሳቅም ጊዜ ጥርስን ፍግግ ፍግግ እያደረጉ መሳቅ ነው እንጂ በውጭ እስቲሰማ ድረስ እተንከተከቱ መሣቅ አይገባም፡፡

56፶፬ በማናቸውም ጊዜ ቢሆን በመሸታ ቤትና በጋለሞታ ሰፈር ተቀምጦ መታየት ትልቅ ነውር ነው፡፡

57፶፭ ባካሄድም ባቀማመጥማ ጊዜ ባለማዕርጉን ማክበር ነው እንጂ ትንሽ ማዕረግ ያለው ትልቅ ማዕረግ ያለውን መቅደም አይገባም፡፡

58፶፮ በንግግር ጊዜ የተጠየቀው ሰው ሳይናገር ያልተጠየቀው ሰው ለመናገር አይገባውም፡፡ በነገሩም መካከል ማሰናከል አይገባም፡፡

© Centre français des études éthiopiennes, 1993

Conditions d’utilisation : http://www.openedition.org/6540

Acheter

Rechercher dans OpenEdition Search

Vous allez être redirigé vers OpenEdition Search