Versione classicaVersione mobile

Bulletin de la Maison des études éthiopiennes | Novembre 1993. N°3

 | 
Jacques Bureau

Ancient Churches in Tchaqata

ዘጋስጫ አባ ጊዎርጊስ ታሪክ

ደመቀ አዳነ ተሰማ

Testo integrale

1የሚገኝበት ስፍራ ወሎ ክፍለ ሀገር ቦረና አውራጃ ከለላ ወረዳ በ 052 ጋስጫ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ክልል ውስጥ ነው፡፡ ጎረቤት ከሆነው ከደብረሴና ወረዳ ርዕሰ ከተማ ከወግዲ እስከ ገዳሙ ድረስ ያለው ርቀት ልብና ሳንባ አቅምና ጉልበትን የሚፈትን አቀበት ቁልቁለትና ጢሻ የበዛበት አስቸጋሪ የሆነ ከ 14 ኪ ሜትር ያላነሰ የእግር መንገድ ሲኖረው ይህን ለመጓዝ ከ 6 ሰዓት በላይ ጊዜ ይወስዳል፡፡

2ገዳሙ የሚገኝበት ቦታ በተፈጥሮው እጅግ የሚያስደንቅና አስገራሚ የሆነ ዙሪያውን ክብ ሆኖ የተጠረበ የሚመስል ነጭ ገደል ካለው ከፍተኛ ቦታ ላይ ነው፡፡ ወደ ገዳሙ ለመሄድ የሚያስችለው ጠባብ የሆነች አንድ አስቸጋሪ የተፈጥሮ መንገድ ብቻ ሲሆን ከገደሉ በምዕራብ በኩል ይገኛል፡፡ የመንገዱ አፈጣጠር ገደሉ እየተፈለፈለ እንደ መሰላል በእንጨት እየተረበረበ የተሰራ ሲሆን የመንገዱን ግማሽ 45 ሜትር ያህሉ በዚሁ መሰላል መሰል አሰራር የተሰራ ሆኖ የመሰላሉ መንገድ እንዳለቀ በሳንቃ የተገጠመ በር ተሰርቶ ይታያል፡፡ ይህም ከውስጥ በኩል ሌሊቱን ተቆልፎ ቀን ቀን ብቻ የሚከፈት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው ቀሪው ግማሽ መንገድ በእንጨት ተረብርቦ የተሰራ ሲሆን ወደ ላይ ሽቅብ አንጋጠው ሲመለከቱ በግራ በኩል ያለው ገደል ቁመት እስከ ሰላሳ ሜትር ያህል ሲሆን መንገዱ ከገደሉ ተፈልፍሎ በአንድ ጊዜ አንድ ሰው ብቻ ማስተላለፍ የሚያስችል ጠባብ መንገድ ነው፡፡ በጠቅላላው 90 ሜትር የሚሆነውን መንገድ እንደወጡ የገዳሙ ሜዳማ ስፍራ ይታያል፡፡ የዚህን ሜዳማ መንገድ እንደጀመሩ በቀኝ በኩል አንድ ከሳር ክዳን በአራት መዓዘን ቅርፅ የተሰራች አነስተኛ ቤት ትታያለች አገልግሎትዋም የገዳሙን ደህንነት ለመጠበቅ የሚሰማሩ ዘብ ጠባቂዎች ማረፊያ ናት፡፡

3ይህን እንዳለፉ በዚሁ ሜዳማ በሆነ ቦታ ላይ በአጥር የተከፋፈሉ የመኖሪያ ቤቶችና አንድ ስፋት ያለው ከሳር ክዳን በአካባቢው ነዋሪ ሕዝብ የጋራ ትብብር የተሠራ የእንግዳ ማረፊያ ይገኛል፡፡ የዚህ ገዳም ሜዳማው የቆዳ ስፋት ግማሽ ጋሻ ያህል ሲሆን ከአፋፉ አጠገብ ቆሞ ቁልቁል ወደ መሬት ሲመለከቱ በመካከለኛ ከፍታ ላይ በሚበር አውሮፕላን ውስጥ ተቀምጦ ወደ መሬት ሲያዩ ያለውን እርቀት ያህል ይገመታል፡፡

4ከእንግዳው ማረፊያ ቤት ወደ ምስራቅ የሚወስደውን መንገድ ተከትሎ ግራና ቀኝ የበቀሉትን የተፈጥሮ ዕፅዋቶችን በዓይን አያማተሩና በውበታቸው እየተደሰቱ ትንሽ መንገድ ከተጓዙ በኋላ ወደ መጨረሻው ገደል አፋፍ ሲደረስ ከገደሉ ተፈልፍሎ ቁልቁል የሚወስድ አግድመታማ መንገድ በግምት 15 ሜትር የሚሆነውን ከተጓዙ በኋላ ከአስደናቂው ገዳም በር ይደረሳል፡፡

5ገዳሙ ከዋሻ (ገደል) ተፈልፍሎ ቁልቁል የተሰራና ሁለት በር ያለው ነው አንደኛው ለወንዶች መግቢያ ሲሆን ሁለተኛው ግን ለሴቶች መግቢያ የተዘጋጀ ነው፡፡ በዚሁ በር ገብቶ ባለው የመጀመሪያ ክፍል ውስጥ ከዋሻው ተቀርፆ የወጣ ሁለት ምሰሶ ሲኖረው በሦስት ረድፍ ለመቀመጫ ከዋሻው የተዘጋጁ ደረጃዎች አሉት፡፡ የተዋጣላቸውና የተመልካችን ዓይን የሚስቡ የአባ ጊዮርጊስና የእመቤታችን ማሪያም ፎቶ ተሰቅሎ ይታያል፡፡ በዚህ የመጀመሪያው የዋሻ ውስጥ ክፍል የሚሰጠው አገልግሎት ቅኔና ማሕሌት መቆሚያ ሲሆን ወደ ውስጥና ሁለተኛው ክፍል የሚያስገቡ ከእንጨት መዝጊያ የተሰራላቸው ሦስት በሮች አሉት፡፡ በግራ በኩል ያለው በር አንድ ወጥ በሆነ ቁመቱ 1.5 ሜትር ወርዱ 75 ሳ. ሜትር በሚሆን እንጨት ተገጥሟል፡፡ ከሌሎቹ ልዩ የሆነበትን ሁኔታ አስጎብኝ መነኩሴ እንዲነግሩን ስንጠይቅ በመጸሐፍት አይደገፍ እንጂ ከእየሩሳሌም በመላእክታት ተሰውሮ የመጣና ገዳሙ በተሰራበት ዘመን የተገጠመ ነው የሚል አፈ ታሪክ አለ ብለው አጫወቱን፡፡

የቅድስት ክፍል

6ይህ ክፍል ከላይ በተጠቀሱት 3 በሮች አልፈው ሲገቡ የሚገኝና ከመጀመሪያው የማኅሌትና ቅኔ ማዜማ በስፋት በወርድና ወደላይ ባለው ከፍታ የተለየና ብልጫ ያለው ይሁን እንጂ እንደመጀመሪያው ሁሉ ትልልቅ ሁለት የድንጋይ ምሶሶዎች አሉት፡፡ ወደ ውስጥ ለሚገባ ሰው በግራ በኩል ሳንቃ (መዝጊያ) የተገጠመላቸው ሁለት በራፎች ሲኖሩት በእነዚሁ በሮች ብርሀን ከውጭ ወደ ውስጥ የሚገባ ሲሆን ወጥተው ሲሄዱ የተለያዩ ትርፆችና መጠን ያላቸው የፀሎት ማድረጊያና አንደኛው ልዩ ዋሻ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህ ልዩ የዋሻ ክፍል ጠበብ ያለ ሆኖ ለአንድ ሰው መቀመጫ የምትሆን ደረጃ መሰል ዙሪያዋን በቀስት መንበር ቅርፅ የተከበበች ናት፡፡ የምን አገልግሎች መስጫ እንደሆነች ሲነግሩን ይህን የምድር ውስጥ ገዳም የሰሩት የአባጊዎርጊስ ድርሰት የሚደርሱባት ክፍል እንደነበረችና አሁን ግን ተጨማሪ የፀሎት ማድረጊያ መሆኗን ገልፀውልናል፡፡

7ከዚህ የድርሰት ክፍል አለፍ ሲሉ ትንሽ መተላለፊያ መንገድ ግራና ቀኝ የሚያስኬድ ቦታ አለው ወደ ቀኝ ሲመለከቱ ከዚሁ የዋሻ አካል የተፈለፈለ የቤተልሔም አገልግሎት የሚሰጥ ክፍል ሲኖር አንድ በር ብቻ አለው፡፡ በግራ በኩል በርካታ በካብ መሰል ጥርብ ድንጋይ የተዘጋ ዋሻ ዓይተን አስጎብኝ መነኮሳትን እንዲያስረዱን ስንጠይቅ በዱሮ ጊዜ በዚሁ ገዳም ሲያገለግሉ ሕይወታቸው ያለፈ የመነኩሳት አፅም የተቀበረበት መሆኑን አስረዱን፡፡

8በወጣንበት በር ተመልሰን ወደ ሁለተኛው ክፍል ስንገባ (ቅድስት ክፍል) በአንደኛው ምሰሶ ስር ደስ የሚያሰኝ ቅርፅ ከእብነ በረድ የተሰራ የጧፍና የሻማ መብራት ማስቀመጫ ተቀምጦ ይታያል ይህም ለብዙ ዘመን አገልግሎት የሰጠ መሆኑን መልኩ ታሪኩን ይናገራል፡፡

9በዚሁ ክፍል ውስጥ በምዕራብ በኩል ያለው የዋሻ ውስጥ ግድግዳ ስፋት ያለው ባለሁለት ረድፍ መደርደሪያ መሰል ተፈልፍሎ የተዘጋጀና በርካታ መፅሀፍት ተቀምጠውበት ይታያል፡፡ ለምን የተዘጋጀ መሆኑን ስንጠይቅ በውስጡ የበርካታ መነኩሳት አፅም የተቀበረበት መቃብር እንደነበር አስረዱን በዚህ ክፍል ውስጥ የቅዳሴ ስራ የሚከናወንበት የቅድስት ክፍል ነው፡፡

10ፊት ለፊት ስንመለከት ረጅምና ጥሩ መልክ ያለው መጋረጃ ተጋርዶ ተመለከትን መጋረጃው ሲገለጥ በር ያልተገጠመላቸው ከዋሻው ተፈልፍለው የተቀረፁ 3 በሮች አሉት እነዚህም ወደ ሶስተኛው ክፍል የሚያሳልፉ በሮች ናቸው፡፡

የቅዳሴ ክፍል

11ይህ የመጨረሻው የቅዳሴ ክፍል ከሁሉም የተለየ ስፋትና ትልቅነት ሲኖረው ባለአንድ ምሰሶ ብቻ ነው የአባጊዎርጊስ ፅላት በዚሁ ክፍል ይገኛል፡፡ ከዚህ ክፍል በደቡበ ምእራብ አቅጣጫ ወይም ከውጭ ለሚገባ ሰው በቀኝ በኩል በግምት ከግድግዳው ቁመት 8 ሜትር ያህል ከፍ ብሎ አንድ የመስኮት ቅርፅ ያለው ክፍት ቦታ ይታያል፡፡ ውስጡ አነስተኛና ክብ መሰል ቅርፅ ያለው ነው፡፡ አገልግሎቱም ለዚሁ ገዳም ታቦት የሚውሉ የምስጢር ዕቃዎች በመሰላል እየወጡ የሚያስቀምጡበት ነው፡፡ በዚሁ መስኮት መሰል በር ስር ከወለሉ ጋር የተያያዘ ከእንጨትና ከድንጋይ የተዘጋጀ ገንዳ መሰል ቅርፅ ያለው በትልቁ ተሰርቶ ይታያል፡፡ ይህም በዱሮ ዘመን የመነኩሳት አፅም ማስቀመጫ የነበረና ከላይ ክዳን ጭምር የነበረው ሲሆን አሁን ግን አፅሙ ተለቅሞ በሌላ ዋሻ የተቀበረ በመሆኑ አገልግሎት የሌለው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡

12ይህ የአባጊዎርጊስ ገዳም ጥንታዊነት ያለውና በአሁኑ ሰዓት ድንግል ቄስ መነኩሳትና ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ዳቆኖች የሚቀድሱበት በዓመት ሁለት ጊዜ ያውም ሐምሌ 7 ቀንና ጥቅምት 3 ቀን የስላሴና የባታ ዓመታዊ ክብረ በዓል ከተለያዩ ቦታ በሚመጡ ምዕመናን በድምቀት የሚከበርበት ታላቅ ገዳም ነው፡፡ የገዳሙ የውስጥ ሁኔታ የሚደረግለት እንክብካቤ በጥሩ ጅምር ላይ ይገኛል፡፡ ይሄውም በዚያው ደብር አናት ላይ ከሚገኝ ነጭ ኖራ መሰል አፈር ተቀብቶ ቢታይ እጅግ የሚያስደስትና ባለቤት ያለው መሆኑን መገመት ያስችላል፡፡

የገዳሙ አምባ

13በዚህ ገዳም በሚገኝበት ክብ መሰል አምባ ላይ የተለያዩ ሁኔታዎችን ለማዬት ችለናል ከእነዚህም አገልግሎት የሚሰጡ 5 የውሀ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶች አንድ በጣም ትልቅና የውስጥ ጥልቀቱ 4 ሜትር ስፋቱ 20 ሜትር ያህል የሚሆን ክብ መሰል የውሀ ማጠራቀሚያ ኩሬ ይገኛል፡፡ ሁሉም ውሀ የያዘ ሲሆን ውሀውን ሲመለከቱት አረንጓዴ መልክ ይምሰል እንጂ በብርጭቆ ውስጥ ሲያዩት ግን ንፁህ የጠራ ውሀ መልክ አለው፡፡ ይህ የጉድጓድና ኩሬ ውስጥ ውሀ ሲጠጡት የሚጣፍጥና የውስጥ ደዌ በሽታን የሚያላቅቅ ነው፡፡ በዚሁ አምባ ላይ የሚኖሩት መነኮሳት ለመጠጥና ለመታጠቢያነት የሚጠቀሙት ከእነዚሁ የጉድጓድና ኩሬ ለተለያዩ አገልግሎቶች በማከፋፈል ይገለገላሉ፡፡

14ከአምስቱ የውሀ ጉድጓዶች አንደኛው የተለየ ሁኔታ ይታይበታል ይህም አባጊዎርጊስ ሌሎቹን ጉድጓዶችና ኩሬ ባዘጋጁበት ጊዜ ለምን ጀምረው እንደተውት ሳይታወቅ በትንሹ ቆፍረውት ስለነበር መምህር ጥዑመልሳን የተባሉ በ1 የ403 ዓ.ም ገደማ ለውሀ ማጠራቀሚያ ብለው ሲቆፍሩ የባሰ ውሀው እየደረቀና ጉድጓዱም ጥልቀቱ እየራቀ በመሄዱ አሁን የሚሰጠው ጥቅም ከሌሎች በጣም አነስተኛ ነው፡፡

15በዚህ አምባ ላይ የሚበቅሉት ዕፅዋቶች ቅንጭብ፣ ቀልቀልሻ፣ ክትክታ፣ ወይራ፣ ደደሆ፣ ግራር፣ ሸንበቆ፣ ባህር ቁልቋል፣ ረጅም ቁልቋል፣ ለንቋጣ፣ ዝደም ሲሆኑ የቦታው የአየር ፀባይ ሞቃታማ ወይናደጋ ነው፡፡

16ቀደም ሲል በዚህ አምባ ላይ ይኖሩ የነበሩት መነኩሳትና ዳቆናት በገዳሙ 50 ጋሻ የእርሻ መሬት ግቢ እየተጠቀሙ 160 ያህል ይኖሩ እንደነበርና የገዳሙ ንብረት የሆኑ የቀንድ ከብት እርባታ ጭምር በፊት ይካሄድ ነበር አሁን ግን እስከ 95 የሚደርስ ብቻ በአምባው ላይ ሲኖሩ ቁጥራቸውም ሊቀንስ የቻለው መሬትን ለሰፊው ሕዝብ ያደረገው ታሪካዊ አዋጅ ከወጣና ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ ቀድሞ ያገኙት የነበረው ጥቅም ስለቀነሰ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተሰደዱ ከመሆኑም አሁንም ካሉትና ሰርተው መብላት የማይችሉት ደካማ መነኮሳት በአምባው ላይ ከሚበቅለው ባህረ ቁልቋል ፍሬ እየበሉ የሚኖሩ መሆናቸውን ለማስረዳት ችለዋል፡፡

17በዚሁ አምባ ላይ ከቀርቀሮ የተሰራ የግንብ ቤት አለ፡ አገልግሎቱም የገዳሙ የቅዳሴ ማከናወኛ ንብረቶች ማስቀመጫ የዕቃ ቤት ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ቁመቱ 2 ሜትር ተኩል የሚሆን መጠነኛ ውፍረት ያለው ጥቁር ድንጋይ በሁለት አነስተኛ ድንጋዮች ላይ ተጋድሞ ተመለከትን ለምን እንደተቀመጠ ስንጠይቅ አመጣጡ በደብረሲና ወረዳ በ04 ደብረፅጌ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ቆላማ ስፍራ ውስጥ ከሚገኘው ከአባ ፅጌ ድንግል ጥንታዊ ገዳም ወደዚህ ጋስጫ ስላሴ ገዳም በሚወስደው መንገድ መካከል ያለውን የወለቃን ወንዝ ለመሻገር በአባ ጊዮርጊስ የተሰራውንና አሁን የተፈጥሮ ድልድይ የሚባለውን ሰይጣን ሊያፈርሰው አባጊዎርጊስ ደርሰው በአንካሴ ከወጉት በኋላ ያፈረሰውን ድንጋይ አሸክመው ወደ ጋስጫ ስላሴ ሲወስዱት ወደ አምባው በሚያስወጣው አስቸጋሪ መንገድ ላይ ሲደርሱ ሰይጣኑ አልችል በማለት ሲጥለው ለሁለት በመፈርከሱ እንደገና ረጅሙን ድንጋይ አሸክመው አሁን የተቀመጠበት ቦታ ላይ ሲደርስ አውርደውት የተቀመጠ መሆኑን በመፀሀፍና በገዳሙ ውስጥ ባለው ስዕል የተደገፈ ታሪክ እንዳለ የተገነዘብንና አቀበታማው መንገድ ላይ የተሰበረውን የዚሁ ድንጋይ ክፋይ በዓይን ተመልክተናል፡፡ ይህ ድንጋይ በአሁኑ ሰዓት የሚሰጠው አገልግሎት ለመቁንን ማለትም ለግብር፣ ለቅዳሴ፣ ለለቅሶና ለመነኮሳቱ ስብሰባ የሚጠራሩበት የድንጋይ ደወል ሲሆን ድምፁም ጥሩ መረዋና እንደብረት የሚያቃጭል ነው፡፡

18በዚህ አምባ ዙሪያ ታላላቅ የመቃብር ዋሻዎችና ያልተደረሰባቸው ማለትም በውስጣቸው ምን እንደያዙ ምስጢሩ ያልተፈታላቸው ዋሻዎች ይገኛሉ እንዲሁም 3 ዓይነት የተለያዩ ቀለማት ያላቸውና እንደሲሚንቶ የሚያገለግሉ አፈሮች ይገኛሉ፡፡

19ከዚህ አምባ ስር ባለውና አልፎ አልፎ ተሰባስቦ የሚታየው መንደር የሚኖሩት የገዳሙ የቅርብ ጎረቤት ነዋሪዎች 90% ያህሉ የእስልምና ሐይማኖት ተከታይና የመጀመሪያ ቋንቋቸው ኦሮምኛ ተናጋሪ ከመሆናቸውም የሚተዳደሩት በግብርና ስራ ላይ ነው፡፡ ለአባጊዎርጊስ ገዳም ከእምነታቸው ውጭ ቢሆንም ባላቸው የሞቀ ፍቅርና አድናቆት መንገዱን በመጠገን የእንግዳ ማረፊያ ቤት በመስራት በዓመት በዓልና ሌላ ጊዜ ወደ ገዳሙ ለሚመጡ ሰዎች መስተንግዶ በማዘጋጀትና በመሳሰሉት ማኅበራዊ ተግባራት የሚያሳዩት ተሳትፎ አስመስጋኝ ነው፡፡

የገዳሙ ቅርስና ንብረት

20በዚህ ገዳም ውስጥ ጥንታዊነት ያላቸውና ገዳሙን በሰሩት በአባ ጊዮርጊስ የህይወት ዘመን ሲገለገሉባቸው የነበሩና አሁን ከገዳሙ ውስጥ የሚገኙ ቅርሶች የምድር ውስጥ ቤተ መቅደሱን ጨምሮ የብራና ላይ ፅሁፍ ያለባቸው መፃሀፍት ሲኖሩ አባ ጊዮርጊስ የታመመ አሻሽተው ያድኑበትና የሞተ ሰው ያስነሱበት የነበረ የሚገለገሉበት አንድ የነሐስ መስቀል በታሪካዊ ቅርስነቱ ይገኛል፡፡

21ሌላው የገዳሙ ታላቅ ንብረት የምንለው ከቅዳሴ ማከናወኛ የተለያዩ አልባሳትና ሌሎች ንብረቶች እንዳሉ ሆነው የዱሮው የገዳሙ አለቃ የነበሩት መምህር አለሙ የተባሉ ስለ አባ ጊዮርጊስ ገዳም ሁኔታ ከንግስት ዘውዲቱ ፊት ቀርበው በማስረዳታቸው የተለያዩ መጠን ያላቸው ሁለት የመዳብ ጎላ ብረት ድስት መሰል ለስጋና ለንፍሮ መቀቀያ የሚሆንና የብር መስቀል ባለ መፃር ጭምር በእርዳታ በማግኘታቸው በአሁኑ ሰዓት የገዳሙ ንብረት ሆነው ይገኛሉ፡፡

የአባ ጊዮርጊስ አጭር የህይወት ታሪክ

22ይህን ገዳም የሰሩት አባ ጊዮርጊስ የተባሉት የተወለዱት ጥንት ሀገር ለኮመልዛ ይባል በነበረው ዛሬ ወሎ ክፍለ ሀገር ውስጥ በሚገኘው ቀድሞ ምድረ አምሀራ ዛሬ ቦረና አውራጃ ውስጥ ከላላ ገፈርስ ወረዳ ቦተርና ወለቃ በሚባሉ ወንዞች መካከል ባለች ልዩ ስሟ ሽግላ ከተባለች ስፍራ ከአባታቸው ህዝብ ጽዮንና ከእናታቸው እምነ ጽዮን ተወለዱ አባታቸውና እናታቸው እርሳቸውን ከመውለዳቸው በፊት መካን ስለነበሩ በፀሎትና በስለት የተወለዱ በመሆናቸው ለአቅመ ትምህርት ሲደርሱ አባታቸው ህዝብ ፅዮን ሐይቅ እስጢፋኖስ ከሚባለው ገዳም ሠርቀ ብርሃን ለሚባሉ መምህር ያስተምሩልኝ ብለው ሰጥተዋቸው ለ7 ዓመት ያህል ቆይተው ፊደል እንኳ ለመቁጠር ባለመቻላቸው ከብዙ ድካምና ፀሎት በኋላ ትምህርት ተገልጦላቸው ወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል አውራጃ ሐይቅ ገዳም ባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ገነት ብርሃን የምትባለውን በስሟ ደርሰዋል፡፡

23በዚህም ግጠበወ ጊወርጊስ አምአጥባት ስዕላ ለማርያም ወውኅዞ ሎቱ አምአጥባት ሰዕላ ለማርያም ወውኅዘሎቱ አምአጥባቲሀ ሀሌብ ዘመንከር ጣዕሙ አድገብቶ ወአርወየተ አምአጥባቲሀ ሀሌብ ዘመንከር ጣዕሙ አድገብቶ ወአርወየተ ወይዕተ ሶቤ ተፈስህ ጊዮርጊስ በመንፈስ ቅዱስ ወደረሰ ለቲ መፅሀፈ ጥኃት ብርሃን ዞይስመይጎ ተብሎ በገደሉ ውስጥ ተፅፎ ይገኛል፡፡

24ይህንንም የድጓ መምህራን በዜማ ቀርፀው አዜሙት ለጥቅምት 3 ቀን ለበአለ ንግሳቸው ዜማ ሆኖ እየተዘመረ ይኖራል፡፡ 2ኛ መፅሀፈ አርጋኖ 3ኛ አንዚራ ስብሀት 4ኛ ህወተ ማርያም 5ኛ መፅሀፈ ብርሀን 6ኛ መፅሀፈ ምስጢር በ81 መፃሀፍት ያለውን የሀይማኖት ምስጢር አጠቃሎ የያዘውን የደረሱ ሲሆን ይህም ሲፃፍ የዘመኑን ንጉሥ አፄ ይስሀቅ አምስት ፀሐፊዎች እንደነበርና ንጉሱ ከአባ ጊዮርጊስ መፃሀፍት አፈጋኖን በመጀመሪያ የወርቅ ቀለም አፅፈው ሲፀልዩበት ኖረዋል 7ኛ ውዳሴ መስቀል 8ኛ ተአምኖ ቅዱሳን 9ኛ የነቢያትና የሀዋሪያት የፃድቃንና የሰማዕታት የመላዕክታትና የሊቃነ መላዕክት ውዳሴ የምስጋና ሰላምታ የሚባለውን መፅሀፍ 10ኛ ፀሎተ ፊትቶ የተሰኙ መፀሀፍቶችን በርካታ ፀሎቶችን የደረሱ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሊቅ እንደነበር ይጠቁማል፡፡

25ስለ አባጊወርጊስ አጠቃላይ ታሪክ ያውቃሉ ከሚባሉና ዛሬ በህይወት ካሉ ሊቃውንት መምህር ተስፋ ወርቅነህ የተባሉ በአዲስ አበባ ገነት እየሱስ ቤተ ክርስቲያን ክልል ውስጥ ያሉና በፊት በቤተክህነት መፃህፍት አሳታሚነት ስራ ላይ አሁን በጡረታ የተገለሉ በመኖራቸው ጠቃሚ የታሪክ መንገዶች ሊያመለክቱ እንደሚችሉ በህይወት እንዳሉ መጠቀሙ የተሻለ መሆኑን እጠቁማለሁ፡፡

ማጠቃለያ

26ይህ ረጅም ዕድሜ ያለው ገዳም ዛሬም ቢሆን በአካባቢው ባሉ ሰዎች መጠነኛ እንክብካቤ በአቅም አንጻር የሚደረግለት ቢሆንም በዚሁ በቃ የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህን የመሰለ ጥንታዊ የምድር ውስጥ ቤተ መቅደስ በታሪካዊነቱ ለመጭውና ለዛሬው ትውልድ የሚያስተላልፈው ገና ያልተደረሰበት ምስጢር የሚኖረውና በጥንታዊ ቅርስነት ሊቀጥል የሚገባው መሆን አለበት፡፡

27በሌላ መልኩ ዛሬ ገዳሙን እንደ ግል ንብረታቸው በመቁጠር በማገልገል ላይ ያሉት መነኮሳትና ዳቆናት የዕለት ኑሯቸውን በመጠኑም ቢሆን አሻሽለው የጀመሩትን ግልጋሎት እንዲቀጥሉና ተተኪ እንዲያገኙ የሚያስችል የስራ መስክና የገቢ ምንጭ በምን መልክ ሊያገኙና ሊመቻች የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ቅድመ ጥናትና ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡

28ዛሬ የአንዳንድ ሀገሮች የገቢ ምንጫቸው ዳብሮ ከሚገኝበት አንዱ ታሪካዊ የሆኑ ቅርሶችን ለመጎብኘት ከሚመጡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ከሚያገኙት ገንዘብ መሆኑ ምሣሌ የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ይህ ገዳም የተጀመረው የመኪና መንገድ ተጠግኖ ቢሰራና ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ተመቻችተው የባለሙያዎችና የታሪክ ሙሁራን ዓይን ቢያርፍበት እንዲሁም የመንግስት ትኩረት ጅምሩን ቢያጠናክር የውጭ ቱሪስቶችን ዓይን የሚስብ የአካባቢውን ህብረተሰብ የኑሮ ደረጃ በፍጥነት ሊለወጥ የሚችል ይልቁንም የእንጨት ፍሬ እየለቀሙ የሚኖሩትን መነኮሳት ችግር ጨርሶ ሊቀርፍ የሚያስችል ምክንያት ከመሆኑም የሀገራችን የስልጣኔ ውጥን ጥንታዊነት ያለው መሆኑን ለዓለም የምናሳውቅበት ታሪካዊ ምስክር ሊሆን እንደሚችል ግምትና የግል አስተያየት አለኝ፡፡

የገዛዛ አቦ ደብር

29ይህ ደብር በወሎ ክፍለ ሀገር ቦረና አውራጃ ደብረሲና ወረዳ 018 ከራባ ጉዳና ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ክልል ውስጥ ልዩ ስፍራው የገዛዛ ከተባለ ቦታ ላይ የሚገኝ ደብር ሲሆን በምስራቅ ከ021 አዋዮ ኩሙዮ ቀበሌ በምዕራብ ከ017 አበርጋ ጊወርጊስ ቀበሌ በደቡብ ከ020 አበይጉርባ ቀበሌ በሰሜን ከጣቀት ወንዝ የሚዋሰን ከገደላማ ቦታ ላይ የሚገኝ አስደናቂ ታሪካዊ ደብር ነው፡፡

30ደብሩ ከሚገኝበት ወረዳ ርዕስ ከተማ ከሆነችው ከወግድ እስከዚህ ቦታ ድረስ ያለው የመንገድ ርቀት በኪሎ ሜትር ሲገመት ከ34 ኪሎ ሜትር ያላነሰ ሲሆን ከዚህ መንገድ 28 ኪሎ ሜትር ያህል የመኪና መንገድ ለበጋ ወራት ብቻ የሚያገለግል ተሰርቶ አገልግሎት ሲሰጥ ቀሪው 6 ኪሎ ሜትር ያህሉ ደግሞ ከ1 ሰዓት የእግር ጉዞ በኋላ ተጠናቆ ይደረሳል የመንገዱ ሁኔታ ግን አቀበትና ቁልቁለት በመጠኑ ይኖራል፡፡

31ወደ ደብሩ አካባቢ ከደረሱ በኋላ ከገደሉ የተፈለፈለው ህንፃ ለመግባት በሁለት በኩል የሚወስድ መንገድ ሲኖር አንደኛው በምዕራብ በኩል ሲሄዱ ወደ ምስራቅ የሚወስደውን አግድመት መንገድ ሲጀምሩ ከገደል ተፈልፍሎ ለሰንበቴ እድምተኞች መጠጫ የሚያገለግለውን ሰፊ ዋሻና በበሩ አካባቢ በበቀሉ የቅንጭብ ዛሮች የደመቀውን ተጨማሪ የማኅበርተኛውን መቀመጫ በመካከሉ ካለፉ በኋላ ወደ ደብሩ ህንፃ የሚወስድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በቀጥታ ከላይ እንደወረዱ ትንሿን አቀበት መጥተው የመጫዎቻና የመነኩሴዎች ማደሪያ ዋሻ መካከል አልፎ በደብሩ ህንፃ አናት ላይ ቁልቁለቱን ሲወርዱ ይገኛል፡፡

32ወደ ውስጥ የሚያስገባው አንድ በር በቁልፍ የተዘጋ ሲሆን ከመግባት በፊት ቆሞ ወደ ላይ አንጋጠው ሲመለከቱ ቀጥ ያለና ርዝመቱ ከ2500 ሜትር ያላነሰ ገደል የባህረ ቁልቋል ረጅም ቁልቋል ክትክታ ትለም ኮምበል ቅንጭብ ደደሆና ሰንበሌጥ ሳር የመሳሰሉት በቅለው ልዩ የተፈጥሮን ውበት ያንፀባርቃሉ በምስራቅ በኩል ያለው የዚሁ ገደል ግማሽ ክፍል አካል በተቃራኒው ሲመለከቱት ያለአንዳች ዕፅዋት ቀይአፈሩ ብቻ እርቃኑን ይታያል፡፡ ይህ የደብሩ ህንፃ ካለበት በታች ደግሞ ቁልቁል ሲመለከቱ በጣም ረጅም ገደል ሲሆን ካለችው ጠባብ የእግር መንገድ በስህተት እልፍ ካለ እንደወረደ መቅረት ነው፡፡ ይህን ችግር በመጠኑም ለማቃለል የሚያግዝ የተለያዩ ዕፅዋቶች እንደ አጥር ተጠጋግተው ቆመው ስለሚታዩ ስጋቱ ይቀንሳል፡፡

33ወደ ደብረ ህንጻ ከመግባታችን በፊት በግራ በኩል ትንሽ አለፍ ብሎ በእንጨት የተገደገደ ነገር ከዋሻው ተጠግቶ ይታያል፡፡ ቀርበው ሲመለከቱ ውስጡ መጠነኛ ወርድና ቁመት ስፋት ያለው ዋሻ ሲሆን አንድ የድንጋይ ወፍጮ በውስጡ ተተክሏል፡፡ ለደብረ የመቀደሻ ግብር ስንዴ መፍጫና አሁንም አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ያለ አስጎብኝ ማወቁ ጊዜ አይወስድም፡፡

34ዋናው በሩ ተከፍቶ ወደ ውስጥ ሲገቡ ከፎቅ ወደ ምድር ቤት እንደሚወርድ ያህል ከገደሉ እየተፈለፈለ ስፋት ባለው መንገድ ቁልቁል ሲወርዱ ትንሽ ድልድል ካለች የገደሉ እምብርት ቦታ ላይ ይደረሳል፡፡

35ወደ ቀኝ በኩል ሲመለከቱ ወደ ዋናው ህንጻ የሚያስገቡ ሁለት ከገደሉ ተፈልፍለው የተቀረፁ በር ሲታይ የመጀመሪያው በር መዝጊ ሲኖረው ሁለተኛው ግን ክፍትና መዝጊያ አልባ የሆነ ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት በሮች መካከል ትልቅ የብረት ደወል በሁለት እንጨት መካከል በተጋደመ እንጨት ተንጠልጥሏል፡፡

ማኅሌትና ቅኔ

36በመጀመሪያዎቹ ሁለት በሮች ሲገቡ የሚገኘው ክፍል የማኅሌትና ቅኔ አገልግሎት መስጫ ክፍል ነው፡፡ ይህ ክፍል የውስጡ ቅርፅ ክብ መሰል ሆኖ ከላይ አናቱ የተስተካከለና አራት ማዕዘን ቅርፅ ባላቸውና ከገደሉ ተቀርፀው በወጡ 3 ምሰሶዎች የተደገፈ ነው አሰራሩ እጅግ የሚያስደንቅ ሲሆን የግድግዳው ተስተካክሎ ማየት ከዘመኑ አሸዋ ግርፍ ቤት ማመሳሰሉ ይመረጣል፡፡ ከግድግዳው ግማሽ ወገብ በላይ ዙሪያውን በተለያዩ የአፈር ቀለማት ቅብ የተሰሩ የመላዕክታት የአንበሳ የበሬ የነብር የፈረስ ምስል ተሰርተው ይታያሉ፡፡ የእነዚህ ምስሎች ዕድሜ ከአቀራረፃቸው አንፃር ሲታይ የህንፃውን ዕድሜ ያህል እንደሆነ ይገመታል፡፡

37ባሉት ደጋፊ ምሰሶዎች መካከለኛው በአንደኛው ጎኑ ውስጡ የተቦረቦረና ክፍት ቦታ ያለው ሲሆን በርካታ መቋሚያዎች ተደግፈው ቆመዋል፡፡ አገልግሎቱም የመቋሚያ ማከማቻ ነው፡፡ በዚሁ ምሰሶ ግማሽ ቦታ ላይ ወጣ ብሎ የተሰራ ጌጥ መሰል ድንጋይ ባላው ላይ ከእብነበረድ የተቀረፀ የሻማና የጧፍ መብራት ማስቀመጫ ይታያል፡፡

38በዚሁ የመጀመሪያ ክፍል ውስጥ በትልቅ ጨርቅ ላይ የአባ ገብረ እንድሪያስ መነኮሳት ዘብሔረ ጫቀታ ያፀደቁ ነፍሶችን በቀስተ ደመና ይዘውና አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ዘብሔረ ገዛዛ አውራ ዶሮ መሰል መብረቅ በብረት ልጓም ይዘው ጋልበውት የሚያሳይ ምስል በአለቃ አየለ የተሰራ ተሰቅሎ ሲታይ በመጠኑም ቢሆን ለክፍሉ የውበት ሺታን የሰጠ ከመሆኑም የቀድሞ ሰአሊያኖች በተፈጥሮ ባላቸው እውቀት ብቻ በመጠቀም ለገዳማትና ደብረ መንፈሳዊ ምስሎችን በራሳቸው ፈጠራ በቀመሙት ቀለማት አስጊጠው ለእይታ ለማብቃት በሚያደርጉት ጥረት ይህን የመሰለና በታሪካዊነቱ ሊወደስና እንክብካቤ ሊደረግለት የሚገባውን ቅርስ ጥለው ማለፋቸውን እንደተገነዘብን ከመቻላችን የዘመኑ ትውልድ ባለበት አደራ ከኋላችን ለሚከተለው ትውልድ ነባር ቅርሶችን ጠብቆ ለትሩፋት ከማብቃት ባሻገር አዳዲስ ስራዎችን ጥለን ማለፍ እንዳለብን ጠንቅቀን እንድናውቅ ይቀሰቅሳል፡፡ ከዚሁ ስዕል በተጨማሪም ሌሎች የቅዱሳንና መላዕክታት ምስሎች ይታያሉ ከዚህ የመጀመሪያ ክፍል ፊት ለፊት ሲመለከቱ አንድ ባለሁለት ተካፋች መዝጊያ ያለውና መዝጊያ ሳይኖረው በትንሽ መጋረጃ የተሸፈነ ሁለት በር ሲኖረው ወደ ቅድስት ክፍሉ የሚያስገባ ነው፡፡

የቅድስት ክፍል

39ይህ የቅድስት ክፍል ከመጀመሪያው ማኅሌትና ቅኔ አልፎ የሚገኝ ሁለተኛው ክፍልና የቅዳሴ ተግባር ማከናወኛ ክፍል ነው፡፡ ይህ ክፍል የውስጥ አሠራሩ ክብ መሰል ቅርፅ መኖሩ እንደመጀመሪያው ክፍል ሲሆን አራት ማዕዘን ቅርፅ ባላቸው አራት የድንጋይ ምሰሶዎች ደግፈው ቆመዋል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የመድሀኒዓለምና የአቦ ታቦት በደባልነት ተቀምጦበታል ከዚሁ ክፍል ውስጥ በስተምዕራብ በኩል ወደ ላይ ደረጃ መሰል መወጣጫውን በእግርና በእጅ እየዳሁ ወጥተው ሲቆሙ እንደገና አንድ በር ይገኛል በዚህ በር ወደ ውስጥ ሲመለከቱ ወደታች ዝቅ ያለና መጠነኛ ስፋት ያለው ክብ ዋሻ በበርካታ የሰው አፅም ተሞልቶና ሁለት ትልልቅ የእንጨት ሳጥኖች በውስጣቸው አፅም የተቀመጠበት ይታያል ከእነዚህ ሳጥኖች አንደኛውና ከመግቢያው በር ጥግ በውስጥ በኩል የተቀመጠው የዚሁ ደብር አለቃና ሀላፊ የነበሩት የመሪጌታ ስቡህ መንግሥቱ በ1977 በችግር ምክንያት ህይወታቸው ያለፈው አፅማቸው ያረፈበት መሆኑ ሲታወቅ ሌላው የማን መሆኑ አይታወቅም በአሁኑ ወቅት ግን በዚህ ዋሻ ውስጥ አፅም ማሳረፉ የተከለከለ ነው፡፡ ይህ በሰው አፅም የተሞላ ዋሻ በጥንት ጊዜ ዋና መቀደሻ የነበረና የምስጢር ዕቃዎችና ንዋየ ቅድሳት የሚቀመጥበት እንደነበር ይታወቃል ይህን ዋሻ የውስጡን ገፅታና አፅም የተከማቸበት መሆኑን ለማዬት በበርካታ ሻማና ጧፍ መታገዝ አለበለዚያም በፓውዛ መብራት ካልተጠቀሙ በስተቀር ለማየት አይቻልም፡፡

40ከዚህ ተመልሰው ወደ ምስራቅ በኩል ዞረው ሲመለከቱ ሁለት መስኮት መሰል ቀዳዳዎች ብርሀን ወደውስጥ ማስተላለፍ የሚችሉ ሲታዩ በመጀመሪያው መስኮት ስር ቁመቱና ወርዱ ትንሽ ኖሆ አጎንብሶ ወደ ውጭ ማስወጣትና ማስገባት የሚችል በር ይታያል፡፡ በዚህ በር አልፈው ከሄዱ ውጪ የሚታይን እልፍ ብሎ ከዚሁ ገደል ተፈልፍሎ የተሰራና የቤተልሄም ክፍል ይገኛል፡፡

41በዚህ ቅድስት ክፍል ካሉት አራት የድንጋይ ምሰሶዎች በመጀመሪያው ላይ ቁመቱ ከአንድ ሜትር የሚበልጥ በምሰሶው አንደኛው ማዕዘን መጠን ልክ ከተጠረበ ድንጋይ ተነባብሮ የተገጠመና ከዋናው ምሰሶ ጋር ተጣብቆ የተሰራና ከአናቱ ላይ በተለያዩ ቅርፅ በእንጨት የተቀረፁ ሁለት መስቀሎች ምሰሶውን ተደግፈው ተቀምጠዋል ይህም የሚሰጠው አገልግሎት የመስቀል ማስቀመጫ ነው፡፡ በዚህ ቅድስት ክፍል መግቢያ በር ላይ ቆመው ወደ ደቡብ አቅጣጫ ሲመለከቱ ባለው ግድግዳ በቅስት መልክ ተቀርጾ የተዘጋጀ መንበር ይታያል፡፡

42ይህ የሁለተኛው ክፍል አናቱ የተስተካከለና እንደመጀመሪያው ማኅሌት ክፍል የተመሳሰለ አሰራር ያለው ሲሆን በተለያዩ ቀለማት ተጊጦ የስጋጃ ላይ ቅርፅ አይነት ይታይበታል፡፡ የሁሉም ክፍል አሰራር አንድ የሆነ ከመሆኑም ሌላ ከገደሉ በተፈለፈለ በኋላ ምሰሶዎች ግድግዳውን የውስጡ አናት ለስላሳና እንደ ሲሚንቶ በሚያጣብቅ አፈር የተቀባ ነው፡፡

የደብረ ዝክርና አዲስ ታሪክ

43ደብሩ ቀደም ሲል የመድሃኒዓለም ታቦት ተቀምጦበት ሲሰራ ከቆየ በኋላ በመጨረሻ ግን የአቡነ ተክለሃይማኖት ታቦት በመጨመሩ ይህ በዋናነት የመጀመሪያው የመድሃኒዓለም ቅዱስ በደባልነት እየተሰራበት መሆኑ በዕለቱ ገዳሙን ከፍተው ያስጎበኙን መምሬ ማናዬ ጌታሁን አስረድተውናል፡፡

44በዓመት ሁለት ጊዜ መጋቢት 5 ቀንና ጥቅምት 5 ቀን በታላቅ ድምቀት የሚከበር ኃይማኖታዊ ክብረ በዓል ከሩቅና ከቅርብ በሚሰባሰብ ምዕመናን ሲከበር የቆየና አሁንም በመከበር ላይ ያለ ነው፡፡ በተጨማሪም በየወሩና በየሳምንቱ እሁድ እሁድ የማኅበርና የሰንበቴ በዓል በህዝብ ክርስቲያኑ ተሳትፎ ይከበራል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የደብሩ አገልጋዮች 5 ቄሶችና 10 ዳቆኖች ናቸው፡፡

45የዚህ ደብር የመጠሪያ ስሙ አውራሪስ ጥንት በጎጃም አገር ጠጣ በሚባል ስፍራ ላይ የነበረች የሴት ንግስት ስሟም ግአገዘ ፀሀይ ነገዳይጪ የተባለች ስለነበረች ይህንን ገዳምም በእሷ ስም ተሰይሞ እንደነበርና ለአጠራር አመች ባለመሆኑ ቀስ በቀስ አገዘ የሚለውን ቃል አሁን በሚጠራበት የገዛዛ በሚል መጠሪያ ፀንቷል፡፡

ቅርፅ

46በደብሩ ውስጥ ያሉ የቆዩ ቅርሳቅርሶች ካባ መጎናፀፊያ የአቡነ መንፈስ ቅዱስ የአንድ ወር ቁንፅል ገደል በብራና ከነሐስ የተሰራ መስቀል ፅዋና ቃጭል እንዲሁም የተለያዩ ንዋዬ ቅድሳት ይገኛሉ፡፡

የመዝፈኛ ዋሻ

47ይህ የመዝፈኛ ዋሻ የሚገኘው ከዋናው ደብር አናት ወጥቶ ባለው ቦታ ላይ ሲሆን አሰራሩም በጣም የሚያስደንቅ ነው፡፡ መግቢያው አንድ በርና መዝጊያ የሌለው ሲሆን የውስጥ ሁናቴው ክብ የሳር ቤት ከነባጡ ያለውን ቅርፅ ይመስላል፡፡ ግድግዳውም ሆነ ባጡ ከድንጋይ ተፈልፍሎ የተሰራ ሲሆን ከላይ አናቱ ትንሽ ክፍት ያላት ናት፡፡ በዚህም ብርሀን እንደልብ ይገኛል፡፡ በዚሁ ክፍል ውስጥ ሁለት መስኮቶች በምዕራብ ሰሜን አቅጣጫና በሰሜን በኩል ሲኖረው ሌላ በምስራቅ በኩል ተጀምሮ ያልተጨረሱ መስኮቶች በምዕራብ ሰሜን አቅጣጫና በሰሜን በኩል ሲኖረው ሌላ በምስራቅ በኩል ተጀምሮ ያልተጨረሰ መስኮት ትንሽ ቀዳዳ ያለው ይታያል የዚህ የመጫዎቻ ክፍል የውስጥ ወለል 8 ሜትር ያህል ይሆናል፡፡

48በበዓል ጊዜ የአካባቢው ቆንጆና ጎረምሳ ሲዘፍንና ሲደልቅ ተመልካቹ በአናቱ ላይ ባለችው ክፍት ቦታ ቁልቁል እየተመለከተ ጫዋታውን የሚያደንቅበት ነው፡፡ ጎጂነቱ እየታወቀ ዛሬ ዛሬ ቀረ እንጂ ከዘፈንና ድለቃው በኋላ በከንፈር ወዳጅ መነጣጠቅም ሆነ በሌላ ጠብ አነሳሺ ምክንያት በሚነሳው ጠብ የመግቢያና መውጫው በር አንድ ብቻ በመሆኑ ደህና እረዳትና ሐይል ያለው ወገን ቀድሞ በበር በኩል ከቆሙ አሸናፊም ተሸናፊም ያለገላጋይ እዚያው ውስጥ ሲዋቃ ውሎ ሲደክማቸው የሚማቱበት ብትር ተሰባብሮ ሲያልቅ ይለያዩ ነበር፡፡

የመነኩሴ ዋሻ

49ይህ ዋሻ ከመጫዎቻው ዋሻ ጎን እልፍ ብሎ በምዕራብ አቅጣጫ የሚገኘው ነው፡፡ ይህ ዋሻ መግቢያው በር አንድ የሆነና ውስጡ ክብ ሆኖ ከላይ ሙሉ በሙሉ ክፍት የሆነ ነው፡፡ ወለሉ ወጣ ገባነት ያለውና ተስተካክሎ ያልተሰራ ነው የወለሉ ስፋት 7 ሜትር ተኩል ያህል የግድግዳው ርዝማኔ 6 ሜትር ያህል ይሆናል፡፡ በዚህ አናቱ ባልተገጠመለት ዋሻ በክረምት ጊዜ ዝናብ ሲጥል ወደ ውስጥ ይግባ እንጂ ወዲያውኑ ወደ ውስጥ ሰርጎ ስለሚገባ ውሀ አይቋጥርም በዚሁ ዋሻ ውስጥ በደቡብ አቅጣጫ ባለው ግድግዳ ወደ ውስጥ ተፈልፍሎ የተሰራ ዋሻ ሲኖር ግራና ቀኝ የተጀመሩ የመስኮት ስራ ቅርጾች ይታያል፡፡ በዚህ ሁለተኛ ዋሻ ሲገቡ የደረቀና የተጎዘጎዘ ቅጠላ ቅጠልና በእሳት የተለበለቡ የድንጋይ ጉልቻዎች እንዲሁም ብጥስጣሽ ኬሻዎች ይታያሉ የዋሻው የውስጥ ክፍል በጭስ የጠቆረ ነው፡፡ ይህም የሚሰጠው አገልግሎት ለመነኩሴ ማደሪያነት ነው፡፡ መነኩሴዎች ቀን ቀን በልመና ተግባር ላይ ተሰማርተው ያገኙትን ምግብ ይዘው ተመልሰው የሚያድሩት አሁንም በዚሁ አነስተኛ ዋሻ ውስጥ ነው፡፡

ሌላ የመቃብር ዋሻ

50ይህ ዋሻ ለብቻው ተፈልፍሎ የተዘጋጀ ሲሆን አገልግሎቱም ሰው ሲሞት የሚቀበርበትና አፅሙ ሲደርቅ ወደ ውስጥ የአፅም ማከማቻ መጋዘን ጭምር ዓይነት ያለው ነው፡፡ በውስጡም በርካታ አፅም ተከማችቶ ይገኛል ይህ ዋሻ ለአንድ ሰው ያህል ብቻ የመቃብር ስፍራ ሲኖረው ይህ የተቀበረ አፅም ሳይወጣ ሌላ ሰው ቢሞት አውጭ መሬት ተቀብሮ አፅሙ ሲደርቅ አውጥተው በዚህ ዋሻ ውስጥ ይቀመጣል፡፡ የማንኛውም ክርስቲያን አፅም አሁንም የሚያርፍበት ሲሆን የዘርና የመሳሰሉት ልዩነቶችና አድልዎች አይታዩም፡፡

51ይህ ሁሉ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጥ ደብርና ዋሻ የተሰራው በቅዱስ ላሊበላ የተዘጋጀ ሲሆን በግራኝ መሀመድ ጦርነት ዘመን ለጥቃት ሳይጋለጥ ተከብሮ የቆዬ ጥንታዊ የምድር ውስጥ ደብር ነው፡፡ የዚህን ደብር አሰራር እስካሁን በተገለጸው መሠረት ዘርዝሮ ለንባብ በማቅረብ ቦታውን ላዩ የኅሊና ቁስል ለመቅረፅ ማስቻሉ የቱን ያህል እንደሚከብድ ባይዘነጋም ታሪኩ ተዳፍኖና ተዘንግቶ እንዳይቀር፡፡

52የብዕር አቅጣጫ ሊቀሰርበትና ልዩ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ መሆኑን ከመገንዘብ አንጻር የተደረገ ጅምር ጥረት ነው፡፡

53ይህ ደብር በአሁኑ ሰዓት እራሱን የሚያስተዳድር ከአካባቢው ህዝብ ክርስቲያን ዓመታዊ መዋጮ ከሚያገኘው አነስተኛ ገቢ ብቻ ሲሆን ሌላ ገቢ ሊኖረው ባለመቻሉ ለደብሩ ጥገናና እድሳት የሚያውለው ገንዘብ ስለሌለው ዋናው ህንጻ የመፈራረስ ሁኔታ ይታይበታል፡፡

54ደብሩ አስፈላጊውን የቅዳሴ ተግባር አሁንም እያከናወነ በመሆኑና ተግባሩ ሳይጓደል መቀጠሉን ለህንፃው ተከብሮ መቆየት ምክንያት ስለሚሆን ማበረታቻ የሚሻው ጉዳይ ነው፡፡

55ሌላው ወደዚህ ደብር የሚወስደው የመኪናና የእግር መንገድ ገና ያልተደረሰባቸውና በጥናት ሊደረስባቸው የሚችሉ ጉዳዮች ስለሚኖሩ የሙያተኞችን በጎና ቀና ጥረት ታሪኩ ይማፀናል፡፡

56አሁንም ሁኔታዎች ተመቻችተው ለህንጻው የውስጥ ጥገና ጭምር ተካሄዶለት ከአሁን ከሚገኝበት የተሻለ መልክ እንዲይዝ ቢደረግ ወደፊት ለቱሪስቶች መሳቢያነት ያለው በጎ ጎን ከፊት አቅሙም ያደገ ይሆናል፡፡

57ስለዚህ ዛሬ ነገ ሳይባል ለዚህ ታሪካዊና ጥንታዊ ደብር ደህንነት መጠበቅ ህዝብና መንግሥት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ሊደረግ የሚገባውን በማሰብ በአፈጻፀሙ በኩል ልዩ ትኩረት ቢሰጠው የጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶችን ደህንነትና ጥበቃን መንግስት ኃላፊነት ጭምር ከመወጣት ባሻገር ለመጭው ትውልድ ታሪካዊነቱን ጠብቆ የማቆየቱን አደራ ሙሉ በሙሉ ለመወጣት እንደሚቻል የፀና እምነት ይኖረኛል፡፡

የደብረ ከርቤ ጊወርጊስ ደብር

58ይህ ከመሬት ውስጥ የተሰራ ቤተ መቅደስ በወሎ ክፍለ ሀገር ደቡብ ወሎ ቦረና አውራጃ ደብረሲና ወረዳ 01 ሠርቶ ማሳያ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ክልል ውስጥ ልዩ ቦታው ደብረ ከርቤ ከተባለው ጎን ለጎን ተደጋግፈው ከቆሙት 3 ጎራዎች በመጨረሻው ተራራ ወገብ ላይ የሚገኝ ነው፡፡

59ከወረዳው ርዕሰ ከተማ ለወግዲ በጣም ቅርብ የሆነና ከግማሽ ሰዓት ያላነሰ የሚወስድ አግድመት ቁልቁለትና አቀበት መንገድ ያለበት ይሁን እንጂ አድካሚነቱ ቀላል ነው፡፡ በዚህ በሶስተኛው ተራራ የሚገኘው ከገደል ተፈልፍሎ የተሰራ ቤተ መቅደስ ከመግቢያው በር አጠገብ ቶሞ ቁልቁል ሲመለከቱ አሰራሩ አስጊ የሆነ ገደል ሲኖረው ቅንጭብ፣ ቁልቋል፣ ክትክታ፣ አንብስ፣ ጠንበለል፣ ይሆ የመሳሰሉት ዕፅዋቶች ሸፍነውታል፡፡

60ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያስገቡ በአንድ ረድፍ ላይ ተቀርፀው የተሰሩ 3 በሮች አሉት እንደሌሎች የምድር ውስጥ ቤተ መቅደሶች ቅኔና ማኅሌት ቅድስትና መቅደስ የተለያዩ መጠንና ቅርፅ ያላቸው ተሰርተው ሲታይ በጠቅላላው በስድስት የድንጋይ ምሰሶ ተደግፏል፡፡ የምሰሶዎች ቅርፅ አወጣጥ ከሌሎች የተለየና አስደናቂነት ያለው ነው፡፡ በመጨረሻውና ሶስተኛው መቅደስ ክፍል የሰው አፅም ሲገኝ በሌሎች ክፍሎች ውስጥ ከተነጠፈው የሰሌን ጉዝጓዝ በስተቀር ምንም ቅርስና ንብረት የለም፡፡

አጭር ታሪክ

61ይህ የምድር ውስጥ ቤተ መቅደስ የተሰራው በአበርሀውአፅብሀ ዘመነ መንግሥት ብፁአ አቡነ ያዕቆብ የተባሉ ጻዲቅ የሰሩት ሲሆን ግራኝ መሀመድ አብያተ ክርስቲያናትን በወረራ ሲያጠፋ በመጣ ጊዜ ሸዋ ላይ እንደደረሰ በዚህ ደብረ ከርቤ ብዙ ዲያቆናትን ዳዊት ያስተምሩ የነበሩትና ይህንኑ መቅደስ ገዳም የሰሩት አቡነ ያዕቆብ አንድ ቀን ዳዊት የሚያስተምሩት ተማሪ ጯወወሀበ ምድረ ለአጓሰ አወህያውጯ የሚለውን አረፍተ ነገር ጯወወሀበ ምድረ ለጋሳጯ ብሎ ከመፅሀፉ ላይ ተጽፎ ያዬውን ሲያነብ ሰምተው ፅሁፉንም ሲመለከት ያነበበው ትክክል ስለሆነ ሀገሪቱ የእኛ አይደለችም አጥፊ ታዝቧታል በማለት ተማሪዎቻቸውን አስከትለው በጎንደር አቋርጠው ትግራይ ክፍለ ሀገር አፅቢደራ ስላሴ ከተባለው ገዳም ገብተው ሲያገለግሉ ኖረው እዚያው አርፈዋል፡፡

62ይህንንም ደብር ሐይማኖታዊ ወረራ ይዞ የተነሳው ግራኝ መሀመድ ውስጡን ከአቃጠለ በኋላ በተደረገው ጦርነት 350 መነኮሳትና 3 ጳጳሳት በሐይማኖታቸው ተጋድሎ አድርገው ህይወታቸው በዚሁ ታሪካዊ ቦታ ላይ አልፏል፡፡

63ከዚህ በኋላ ተዳፍኖ ቆይቶ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ደብረ ከርቤ የሚባለው የቤተክርስቲያን ዝርዝር ሁኔታ በፅሁፍ በመገኘቱና አገድፈለግ በመደረጉ ከተገኘ በኋላ የወሎው ገዥ ራስ ሚካኤል ለንጉሥ ምኒልክ አሳስበው ፈቃድ በማግኘታቸው አስደብረው ደብር እንዲሆን ለመተዳደሪያም 4 ጋሻ መሬት ለታቦቱ ሰባት ጋሻ መሬት ለድቁናና ለቅስና ቀዳሾች ስሪት ሰጥተው መምህር ቀለመወርቅ የተባሉትን ለደብሩ ሀላፊ አድርገው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

64በልዑል ራስ ካሣ ገዥነት ወቅት በዚሁ በህንፃው አናት ላይ በበቀለው እንጨት ስራስር ውሀ ገብቶ በማፍሰሱና መፈራረስ በመጀመሩ በውስጡ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ከዚህ ወጥቶ ደጋማው ቦታ ላይ ከግንብና ከሳር ክዳን የተሰራው ቤተክርስቲያን ውስጥ በ1925 ዓ.ም እንደገና የቅዱስ ተግባር እንዲጀመር ተደርጎ ሲሰራበት ፋሺስት ኢጣሊያ ሀገራችንን በወረረች ጊዜ በዚሁ ውስጥ ተቀምጠው የደብሩ ቀደምት ንብረት የነበሩትን አልባሳት ከመንግስት የተሰጠ ነዋይ ቅዱሳት የታሪክ መጻህፍቶች በርካታ ቅርሣቅርሶች ተዘርፈው ተወስደዋል፡፡

65አባ ዴሴ አበጋዝ የተባሉ ባህታዊ የትውልዳቸው ቦታ ወረሄመኖ አውራጃ የሆነ በትግራይ ክፍለ ሀገር አፅበደራ ስላሴ ከተባለው ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲያገለግሉ በነበሩበት ጊዜ ስለ ደብረ ከርቤ ጊዮርጊስ የተጻፈውን ታሪክ አግኝተው በማንበባቸው በታሪኩ መሪነት እዚህ ቦታ መጥተው ብዙ ተማሪዎችን ሲያስተምሩና በቤተ መቅደሱ ሲያገለግሉ ቆይተው መንኩሰው አርፈዋል፡፡

እንክብካቤና እድሳት

66ይህ ዋሻ ውስጥ ቤተ መቅደስ እንደሌሎች ገዳማትና ደብር አገልግሎት ሊሰጥ ያልቻለበት ምክንያት እንደተገለጸው በዝናም ውሀ እየተሸረሸረ መፍረስ መጀመሩና ውሀ በአናቱ ውስጥ ዘልቆ ወደ ውስጥ ስለሚፈስ ነው፡፡ ለዚሁ ታሪካዊና ጥንታዊ የደብር የዛሬው ትውልድ ምን ያስባል ብለን ካለፈው በ1980 ዓ.ም ጀምሮ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ከዚህም የክረምቱን ዝናም ለመቋቋም የአካባቢው ህብረተሰብ በራሱ ፈጠራ በውጭ በኩል ከየዋሻው አናት ጀምሮ በሳር ክዳን ጣራ ተስርቶለት የዝናሙን ውሀ ተቀብሎ ወደ ውጭ እንዲፈስ የሚያስችል ስራ ተሰርቶ ሲታይ ከአካባቢው (ቦታው) ለዚህ ስራ የነበረው አስቸጋሪነት አንፃር ሲታይ ታላቅ ስራ ነው ያሰኛል፡፡ ስለዚህ አሁንም የውስጥ ጥገናና እድሳት የሚያስፈልገው ከመሆኑም ሌላ የውጩ አካል በሳር መሸፈኑ ለጊዜው እንጂ ለቋሚነት መከላከያ ባለመሆኑ ብዙ ጥረትና የተባበረ ጋራ ትኩረትን ይሻል፡፡

ማጠቃለያ

67ይህ ጥንታዊ የምድር ውስጥ ህንፃ ከትውልድ ትውልድ ሲወራረስ የመጣና በዚሁ ቅርስነቱ ተጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ሀብት በመሆኑ ሊተኮርበትና አስፈላጊው ጥገናና እድሳት እንደሚያስፈልገው ይታመናል፡፡ ስለዚህ የአካባቢው ኅብረተሰብ ለዚህ ህንፃ መከበርና ደህንነት መጠበቅ የሚያደርገው የጋራ ጥረት አበጀ የሚያሰኝ ከመሆኑም ጥረቱ እንዲቀጥል ማድረጉ የበለጠ ለህንፃው ደህንነት መጠበቅና እንክብካቤ መሰረት ስለሚሆን መንግሥት ያስፈልጋል ብሎ ያመነበትን እርዳታና ማስተባበር ቢያደርግለት የበለጠ ጠቃሚነት እንዳለሁ እገምታለሁ፡፡ በተጨማሪም ታሪካዊ ደብሩ በታሪካዊነቱ እንዲቆይ ከማድረጉም ባሻገር ለደብሩ መተዳደሪያ ገቢ የሚመቻች ቢሆን የሚሰጠው የሥርዓት ገዳምና ሥርዓት ደብር አገልግሎት እንዲቀጥል ከማስቻሉም ተተኪ አገልጋዮች ጭምር ሊፈሩበት እንደሚችል ሐሳብ አለኝ፡፡

ወለቃ ዘከርያስ ገዳም

68ወለቃ ዘከርያስ ገዳም በወሎ ክፍለ ሀገር ቦረና አውራጃ ደብረሲና ወረዳ 07 በቅፌ ቀበሌ ክልል ውስጥ ሰቃማው ቦታ ላይ ከገደሉ ስር ካለው አካባቢ ይገኛል የሚባል የተዘጋ ገዳም ነው፡፡

69ይህ ገዳም አለበት የሚባለው ቦታ በውል መግቢያው በር ይሄ ነው ተብሎ አይታወቅ እንጂ ጠቋሚ የመሰሉ ምልክቶች ለማየት ተችሏል፡፡ ከእነዚህም አነስተኛ መጠን ያላቸው ሁለት ዋሻዎች ጥንት የዘብ ጠባቂ መቆሚያ ነበሩ የሚባሉ ከዚሁ በቀኝ በኩል በዱሮ ጊዜ የተፃፈ በቅፌ የሚል ከገደሉ ላይ ተፅፎ ሲገኝ ትርጉሙ የስደተኛ ንብረት መሸሸጊያ ማለት ሲሆን በግራ በኩል ሁለት ቦታ ላይ የነበረውን ፅሁፍ በምሳር ተፈቅፍቆ በሰው የጠፋና ምን ተፅፎ እንደነበር አይታወቅም፡፡

70ገዳሙ ጥንታዊ የሆነና አባ ወለቃ ዘካሪያስ እየሱስ የተባሉ ፃዲቅ የሰሩት የምድር ውስጥ ህንፃ ነው፡፡ አዘጋጉም ግራኝ መሀመድ የተባለ የእስላም ንጉሥ ተነስቶ ገዳማትንና ደብርን ያጠፋል የሚሉ ትንቢት ስለሚነገር ይህ ገዳም ለወረራ እንዳይጋለጥ ሲባል በአካባቢው ሰፍረው የነበሩት ክርስቲያኖች ለ1 ዓመት ያህል አፈርና ድንጋይ እያጋዙ ደፈኑት ሲባል በኋላም ገዳሙ እንዲከፈት ጀማል በሻህ የተባለ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ገዳሙ ከተከፈተ የግል ይዞታ መሬታቸው ቃጭል ዞሮበት የገዳሙ ሰሞን መሬት ይሆናል በሚል ፍራቻ ሌሎች የሚያውቁ ሰዎችን ጭምር ቦታውን ለመንግሥትም ሆነ ለማንም እንዳያሳዩ እስከ ልጅ ልጅ የሚደርሱ እርግማን በማውጣታቸው እያወቁት እንደማያውቁት ሆነው ቦታውን ለመጠቆም ማንም ፈቃደኛ አልተገኘም፡፡

71ይህ ገዳም ቢወጣ ይገኛል የሚባል ቅርሥ የወርቅ ካባ የወርቅ ቡችላ የወርቅ መቋሚያ የእየሱስ ታቦት እንዲሁም ከየሹም ወንዝ በመለስ ከወለቃና አባይ ወንዝ መለስ ብለው የጫቃታ አካባቢ ቦታ ከመሬት ውስጥ ተጽፎ የተሸሸገውን የ 44 ገዳማት ጠቃሚ ታሪክ የያዘ የታሪክ መፃህፋትና ሌሎች ቅርሶች ይገኛሉ የሚል አፈታሪክ አለ፡፡

72ስለዚህ ይህን ሁሉ አፈታሪክ እውነታውን ለመመዘን የሚቻለው በሣይንሣዊ ዕውቀት የተካኑ ሙያተኞች ብርቱ ጥረት አድርገውበት የሚገኘው ፍሬ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

73ገዳሙ አለበት የሚባለው ቦታ ዳገታማ የሆነና አፈሩ ድቢሸት ሆኖ የሚያንሸራትት ሲሆን ከበታቹ ትልቅ የዋርካ ዛፍና የተጋደመ ቋጥኝ ድንጋይ ይገኛል በጎን በኩል ከላይ የሚመጣና ለመስኖ አገልግሎት የአካባቢው ገበሬዎች የሚጠቀሙበት ውሀ ይፈሳል፡፡ ይህም የመስኖው ስራ ሊሰፋ የሚችልበት ሁኔታም ቢመቻች ገዳሙን ከመፈለግ ጎን ለጎን ለመሄድ ቢችል አካባቢውም ሊለማ የሚችል ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

74ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የፍለጋው ሁኔታ ከአካባቢው ነዋሪ ሰዎች በተለያዩ የማቅረቢያ ዘዴ በመልቀም ቦታውን በትክክል ለማወቅና ከቁፋሮ በኋላም አለ የተባለውን ገዳምና ቅርፅ ለማግኘት ይቻል ይሆናል የሚል ግምት ይኖረኛል፡፡

75ወደፊት በዚሁ ወረዳ 04 ደብረ ፅጌ ቀበሌ ውስጥ ስለአለውና በአባ ፅጌ ድንግል የተሰራውን ገዳም አይቼ ታሪኩን ለመጻፍ እሞክራለሁ፡፡

Autore

ቦረና መካነሠላም

Il testo e gli altri elementi (illustrazioni, file importati) possono essere utilizzati con OpenEdition Books License, se non diversamente specificato.

Acquista

Cerca su OpenEdition Search

Sarai reindirizzato su OpenEdition Search