Versione classicaVersione mobile

L'Empereur Ménélik et l'Éthiopie | አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ

 | 
Guebrè-Heywèt Baykedagne

አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ

Guebrè-Heywèt Baykedagne

Testo integrale

1እቴጌ ጸሐይቱ

እቴጌ ጸሐይቱ እንደ ሌሎች ሁሉ ንግሥቶች አይደሉም የመከሩት አገር የሚያሳድር የተናገሩት ከምድር ጠብ የማይል ለባላቸው መልካም ደገፋ ለኢትዮጵያ ጋሻ ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር አፈ ወርቅ ገብረ የሱስ፡፡

2አጤ ምኒልክ

ዳግማዊ ምኒልክ በአማን ወልዱ ለሰሎሞን ወልደ ዳዊት ናቸው፡፡ ወይ ግሩም ግሩም ነው ግሩም የግሩም ግሩም፡፡ ሚኒልክ ትበል እንዲህ እናት ስምን መላክ ነው የሚያወጣው፡፡ ምኒልክ ማለት ምን ይልክ ይሆን እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡

እግዚአብሔር እሄው ምኒልክን መርጦ ሒድ ኢትዮጵያ ተጎድታለች የኢትዮጵያም ሰው አልቅሶዋል በሕዝቡ ድንቁርና በዝቶበታልና ሒድ ኢትዮጵያን አይዞሽ በላት የድኃውን እንባ አድርቅለት፡፡ ድንቁርና ጨለማ ነው እውቀት ግን ብርሃን ነውና በኢትዮጵያ ጨለማው እንዲሻል ብርሃን እንዲወጣ ለሕዝቡ የረቀቀው በልብ የጎላው በዓይን እንዲከሰትለት አስተምረው አርመው ጠብቀው ላንተ አይደለም ለኢትዮጵያ ነው ያነገሥሁህ ብሎ ላካቸው፡፡ ዳግማዊ ምኒልክም በተላኩት እሄው ወዲአው ከነገሡ ደኃውን ከባርነት አርነት አወጡ፡፡
ፕሮፌሰር አፈ ወርቅ ገብረ የሱስ፡፡

ሃጸይ ምኒልክን ኢትዮጵያን

3እዚ አብ ታሕቲ ተሐቲሙ ዘሎ ዛንታ ብአቶ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ እተጸሕፈ እዮ፡፡ ቅድም አስተርጓሚ ሀጸይ ምኒልክ ነይሮም እዮም እሞ ካብ ካልኦት ዝሔሸ ብዛዕባ ንብረቶም ገለ ቁሩብ ኬዘንትው ኸአሉ፡፡ ምስ ብዙሐት መኳንንቲ ኢትዮጵያ ድማ አተላለዮ ሰብእዮም፡፡ እዚ ዛንታ እዚ አብ ትሕቲ ስእሊ ንጉስን ንግስትን ኪሕተም ምተገብኦ ነይሩ እንተ ኮነ ግና አይረኸብናዮን ኔርና እሞ ሕጂ አብ መወዳእታ ጌርናዮ፡፡ እዚ አብዛ መጽሐፍ እዚአ ተሐቲሙ ዘሎ ዛንታን ምኽርን ነዞም ሰብ አዛ ሀገር እዚኣ ድቡቅ መምሀሪ መገዲ ሐባሪ ክኾኖም ተስፋ ንገብር አሎና፡፡ አብዚ መጀመርታ ድማ ንምምሳው ሐደ ፈታዊኦም ከም እተጻሕፈ ንርኢ አሎና፡፡

አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ

4ይህንን ከታች የተመለከተው ታሪክ በአቶ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ የተጻፈ ነው፡፡ ቀደም ሲል የአፄ ምኒልክ አስተርጓሚ የነበሩ ናቸውና ራሳቸውን በተመለከተ አንዳንድ ሐሳብ በሌሎች ሳይሆን ራሳቸው ለመተረክ ችለዋል፡፡ እርሳቸው ከብዙ የኢትዮጵያ መኳንንት ጋራ የተዋወቁ ናቸው፡፡ ይህንን ታሪክ በንጉስና ንግስት ስእል ስር ሊታተም በተገባ ነበር ነገር ግን አላገኘነውም ነበርና በመጨረሻ ልናረገው ተገደናል፡፡ በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ታትሞ የሚገኘውን ታሪክና ምክር ለዚች አገር ሰዎች ጥሩ የማስተማሪያ መንገድ ጠቋሚ እንዲሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በዚሁ በመጀመርያው ገጽ ደግሞ አንድ ወዳጃችውን ለማመስገን ብለው የጻፉትን እናያለን፡፡

5ይድረስ

6ካቶ ጳዉሎስ መናመኖ

7ወዳጄ ሆይ፡፡

8እነሆ ከእግዚአብሔር በታች ባንተ ደግነት ከሞት ዳንሁኝ፡፡ በብርቱ ታምሜ ተስፋ ቆርጬ በምጥዋ በሆስፒታል ወድቄ ሳለሁ በገንዘብህ አገዝከኝ፡፡ ለቸሩ ደጃዝማች ገብረ ሥላሴ በመንገርህም የበለጠ የደግነት ስራ አደረግህልኝ፡፡ እነሆም ላገራችን ጥቅም ይሆናል ሲሉ ይህንን ትንሽ ቃል ለመጻፍ በቃሁ፡፡ የተመሰገነልኝም እንደሆነ ምስጋናው ላንተ ነው፡፡ ለኔ ዕድሜ እንዳስጨመርህልኝ አምላክ ረጅም ዕድሜ ይስጥህ፡፡

9ግነትህን እስከ ሞቱ ድረስ ከማይረሳ፡፡

10ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፡፡

11ታሪክን መማር ለሁሉ ሰው ይበጃል ለቤተ መንግሥት መኮንን ግን የግድ ያስፈልጋል የዱሮ ሰዎች ስሕተትንና በጎነትን አይቶ ለመንግሥቱና ላገሩ የሚበጀውን ነገር ያውቅ ዘንድ፡፡ የታሪክ ትምሕርት ግን የሚጠቅም የውነተኛ ታሪክ ትምህርት ሲሆን ነው፡፡ እውነተኛንም ታሪክ ለመጻፍ ቀላል ነገር አይደለም የሚከተሉትን ሶስት የእግዚአብሔር ስጦታዎች ያስፈልገናል፡፡ መጀመርያ ተመልካች ልቦና የተደረገውን ለማስተዋል ሁለተኛ የማያደላ አእምሮ በተደረገው ለመፍረድ ሶስተኛ የጠራ የቋንቋ አገባብ የተመለከቱትንና የፈረዱትን ለማስታወቅ፡፡ ያገራችን የታሪክ ጻፎች ግን በነዚህ ነገሮች ላይ ኃጢአት ይሰራሉ፡፡ በትልቁ ነገር ፈንታ ትንሹን ይመለከታሉ ለእውነት መፍረድንም ትተው በአድልዎ ልባቸውን ያጠባሉ አጻጻፋቸውም ድብልቅልቅ እየሆነ ላንባቢው አይገባም፡፡ ይህም ነገር በቤተ መንግሥትና በየገዳሙ ከሚገኙት ታሪክ ነገሥታት ጥቂት ብራኖች ብናነብ ወድያው ይገለጽልናል የታሪካችንም ጻፎች ሁለት ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ አንዱ ዓይነት የቤተ መንግሥት ሊቃውንት ይባላሉ ማለት እንጀራን ሲፈልጉ ከቤተ መንግሥት ተጠግተው ንጉሡ ያዘዛቸውን የራሱን ውዳሴ ታሪክ ብለው ጽፈው ለኋላው ትውልድ የሚያስቆዩ አቆላማጮች፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ግን መነኮሳት ናቸው፡፡ እነሱም የሚጽፉት ታሪክ አድልዎ ይበዛበታል፡ የራሳቸው እንጅ የሕዝቡን ጥቅምና ጉዳት ከቶ አያቋጥሩምና ስለዚህ የልባቸውን የሚፈጽምላቸው ንጉሥ ቅዱስ ቅዱስ ይሉታል ከድንቁርናቸው ወጥቶ ከፍ ባለ ሕሊና ተመርቶ ስለዜጎች ልማት የሚጥር ግን ርኩስ፡፡ አሁን ጎዳናንና ድልድዮችን ከሚያስበጅ የጥበብንም ማስተማርያ ቤቶች ከሚከፍት ንጉሥ ይልቅ የመንግሥቱን ጉዳይ ሁሉ ረስቶ ከናዝራዊ ከሌላም ዓይነት መኖክሴ የሚውል ሥራ ፈትተው ለሚኖሩቱ መኖኮሳትም ምግብ ብሎ ብዙዎች አገሮች የሚጎልት ንጉሥ በነሱ ዘንድ ይመሰገናል፡፡ ያገራችንም የታሪክ ጻፎች ውዳሴ ከንቱና ስድብ እውነተኛውን ታሪክ አይተው የማይመስለውን ተረት የሚወድ ባይሆን ምንም ባልጎዳነም ነበር፡፡ መጽሐፋቸውንም አንቦ እውነቱን መርምሮ ለማግኘት አእምሮ ላለው ሰው ባላስቸገረውም ነበር፡፡ እጅግ ያሳዝናል እስካሁን ድረስ ያበሾችን ታሪክ በጨለማ ተሸፍነዋልና፡፡

12 አባቶቻችን ከባሕር ማዶ ተሻግረው መጥተው ይህነን አገር ሲያቀኑ ያገኙትን ድካም ከድካሙም በኋላ አክሱማውያን ተብለው የደረሱበትን የክብረት ከፍታ ቀጥለውም በሃይማኖት ልባቸው ተለያይቶ መጀመሪያ አርመኖችና ፈላሾች ሁለተኛም ፈላሾችና ክርስቲያኖች ቆይተውም ክርስቲያኖችና እስላሞች እየተባባሉ እርስ በርሳቸው ተፋጅተው ዝቅ ብሎ ጠፍቶ የነበረው መንግሥታችን ባባ ታጠቅ ቴዎድሮስ ሲታደስ በወሬሳው ካሣም ሲዋሃድ እንዴት እንደነበረ ባባ ዳኘው ምኒልክም እንዴት አርጎ ሰፍቶ እንደረጋ ገልጾ የሚያወጋን የታሪክ ጸሐፊ ከቶ መቸ ይወጣ ይሆን፡፡ ይህ ምኞት ግን እስከ ብዙ ጊዜ ድረስ የሚፈጸም አይመስልም፡፡ አሁን በዘመናችን በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ የሆነውን ነገር እንኳ አጥርተን ለማወቅ ያልተቻለን የዱሮውን አንሻን እስከዛሬ ድረስ እኮ ልከኛ ያጤ ምኒልክ ታሪክ አልተጻፈም፡፡ ነገሥታት በሕይወታቸው ሳሉ ታሪካቸውን ያለ ፍራት የሚጫወቱበት ያርነት ጊዚያት ለአበሻችን ገና አልወጣም፡፡ ደግሞም እንደ አገራችን ሰው ትምህርት የሌለው ሕዝብ እውነቱን ሊሰማ አይወድም ቢሰማም አይገባውም፡፡ አንድ ንጉሥ እንዴህ አርጎ ጥሮ ነገሠ ከነገሠም በኋላ በእንዴህ ያለ ምክንያት ይህንን ፈጸመ ይህነንም ተወ በንዲህ ያለም ነገር ወደቀ ወይም ለማ ከሚሏቸው ይልቅ እገሌ ከሰማይ ወይም ከጠንቋይ እንደዚህ ያለ ትንቢት መጥቶለት ለመንግሥት የተወለደ ሰው መሆኑን አውቆ ታውቆ እገሌና እገሌ ታጠቁለት እገሌና እገሌም ሰይጣን አስቶዋቸው ተዋግተውት አሸነፋቸው ነገሠም ከነገሠም በኋላ እገሌ ቅዱስ ወይም ናዝራዊ መክሮት ይህንን አደረገ ከሰይጣንም ቢፋቀር እንዴህ ያለ ጉዳት ወረደበት በፍካሬ የሱስ የተነባውም ጊዚያቱ ተፈጽሞ ሞተ ብለው ቢዋሹላቸው ይወዳሉ፡፡ ጉልበት የሌለው ብዙ ንጉሥ ኑሮዋል ይኖርም ይሆናል ነገር ግን የታሪካችን ቃል እውነት ከሆነ ዘንድ እንዴሁ በብዙ የቅዱሳንንና ያጋንንትን ርዳታ እንደ ኢትዮጵያችን ነገሥታትና ገዦች የሚያስፈልገው ሰው በዓለሙ ታሪክ ከቶ አልተሰማም፡፡

13 ከዚህ ቀደም የሚወጋውና የተጻፈው ያጤ ምኒልክ ታሪክም ትክክል አይመስልም፡፡ አቶ ገብረ የሱስ አፈ ወርቅ ከጻፉትም መጽሐፍ በቀር ፍሬ የሚገኝበተ ነገር ለሸዋው ንጉሥ ገና አልተጻፈላቸውም፡፡ ያ ካቶ አፈ ወርቅ እጅ ታተመ ታሪክም ቢሆን ምሉ አይዶለም፡፡ ብዙውን ነገር በጨለማነቱ ይተዋል ብዙውንም ነገር ያሳምራል በየዋሁ በጠንካራውም የትግሬ ነገድ ይልቁንም በንደ ወሬሣ ካሣ ያለ አርበኛ ከማንም ሰው እንጅ እንደ አቶ አፈ ወርቅ በሊቅነቱ ከተጠራ ሰው እጅና አፍ ሊወጣ የማይገባው የስድብ ቃል ይገኝበታል፡፡ ዳግማዊ ምኒልክም ለማመስገን ዳግማዊ ዮሐንስን መስደብ የሚያስፈልግ ያስመስላል፡፡ ስለሆነም የትምህርት ወዳጅ የሆነ በመልካም አማርኛም የተጻፈ መጽሐፍንም ማንበብ የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያንን መጽሐፍ ያደረገ አድርጎ ገዝቶ ሊያየው ይገባል፡፡

14እነዚህን ጥቂቶች ቃሎች የሚጽፍ ሰውም ቢሆን ያጤ ምኒልክን ታሪክ አውቃለሁ ብሎ አይመካም ሊጽፍም አይከጅልም፡፡ ከዚህ ቀደም ከተጻፉት ውሸቶች ላይ ሌላ ውሸት ሊጨምር አንዳች ፈቃድ የለውምና፡፡ አሳቡስ ድፍረት ሁኖ እንዳይቆጠርበት ይፈራል እንጅ ዳግማዊ ምኒልክ ስለ ሕዝባቸው ልማትና ትልቅነት ምን እንደጣሩ ምንስ ሳይጥሩ እንደቀሩ ለማመልከት ነው፡፡

15አጤ ምኒልክ በ፲፫ ነሐሴ ፲፰፻፴፭ ዓመተ ምሕረት ባበሻ ቁጥር ባንኮበር ከተማ ከሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮትና ከወይዘሮ እጅግአየሁ ተወለዱ፡፡

16ካጤ ተክለ ጊዮርጊስ ፍጻሜ መንግሥት ጀምሮ አጤ ምኒልክ ተወልደው ያሥራ ሁለት ዓመት ልጅ እስኪሆኑ ድረስ አገራቸው ሸዋ ባላባቶችን እያሰለጠነ ከቀሩት የኢትዮጵያ አውራዶች ተለይቶ ለብቻው መንግሥት አቁሞ ነበር፡፡

17በ፲፰፻፵፯ ዓ.ም ግን ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሙተው ትልቅ ጦርነት ሳይሆን አጤ ቴዎድሮስ አገሩን ወደ መንግሥታቸው ጨመሩት፡፡ አጤ ምኒልክም ከብቁዎች የሸዋ መኳንንት ጋር ተማርከው ወደ በጌምድር መጡ፡፡ የሀያ ዓመት ጎበዝ ሁነው ከድተው ወዳገራቸው እስኪመለሱ ድረስም ባጤ ቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት በክብረት አደጉ፡፡ አጤ ቴዎድሮስ ከሞቱም በኋላ መንግሥት ሊይዙ ጣሩ እንደማይሆንላቸው አይተው ግን ላጤ ዮሐንስ ታጠቁ፡፡ አጤ ዮሐንስም በመጋቢት ፲፰፻፹ ዓ.ም በመተማ ጦርነት ከሞቱ በኋላ የሸዋው ባላባት ወደረኛ የሚሆን ሰው አልተገኘም፡፡ በዚህ ምክንያት በ፳፯ መስከረም ፲፰፻፹፩ ዓ.ም አጤ ምኒልክ የንጉሠ ነገሥትን ዘውድ በንጦጦ በእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ጫኑ፡፡

18ከነገሡ እስከ ዛሬ ያለፈውን ዘመን ብንመለከት እጅግ የታደሉ ንጉሥ እንደሆኑ ይገልጽልናል፡፡ የድላቸውም ኮከብ እስኪታመሙ ድረስ አልተለያቸውም፡፡ እንደነ አጤ ቴዎድሮስ እንደነ አጤ ዮሐንስም ዕድሜያቸውን በድንኳን አላሳለፉትም፡፡ ነገር ግን አንድ ጊዜ በንጦጦ አንድ ጊዜ ባዲስ ዓለም አንድ ጊዜ በአዲስ አበባ በደመቀ ቤተ መንግሥት አርፈው በሰላም ተቀመጡ፡፡ ህውከተኛውም ያበሻ ሕዝብ ሰላማዊ ሆነላቸው አንባቢው በምን ምክንያት ብሎ ይጠይቅ ይሆናል አዲስ የሚበጅ ህግጋት ስላወጡ ወይስ ለሕዝቡ (ላቶ አፈ ወርቅ እንደሚመስላቸው) ትምህርት ስለገለጹለት ይሆንን የሸዋ ሰው አዎን ይላል፡፡ ትግሬውም ባላባቶች እርስ በርሳቸው እየተመቃኙ አስገዟቸው ብሎ ብሎ ያወጋል፡፡ ስሜን በጌምድር ላስታ የጁ ግን ኢቴጌ ጸሐይቱን በማግባታቸው እኛን የሚያህል ኃይለኛ ረዳት ስላገኙ ነው ብሎ ይመካል፡፡ ባጤ ዮሐንስ ጠፍቶ የነበረው ጎጃም በቸርነታቸው ያመካኛል ጋላውም ሁሉን ከሚችል ብርታታቸው የተነሣ ነው ይላል፡፡

19እስኪ የማናቸው ነገድ አሳብ እውነት እንደሆነ እንመርምር፡፡ ጥቂትም ብናስተውል ከትግሮቹና ከሸዎቹ በቀር ሁሉም እውነታቸውን እንደሆነ ይገባናል፡፡ ይልቁንም ጋላ የዳግማዊ ምኒልክን ኃይል ሊፈራ ሥርዓት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ከግራኝ ወዲህ አይታው የማታውቀውን ብርታት ስፋትም አግኝታለች፡፡ ዛሬ መንግሥታችን እንኳን ባገራችን ውስጥ በውጭ ነገሥታትም ቢሆን ኃይሉ ታውቆለታል፡፡ ነገር ግን የጤና መሠረት የሌለው ቤት ብዙ ዕድሜ ያገኛል ተብሎ እንደማይታመን እንዲሁም መንግሥታችን መሠረት ያለው ሥርዓት እስኪያገኝ ድረስ ኃይሉ ብዙ ዓመታት ያቆያል ተብሎ አይታመንለትም፡፡ ይህ ነገር እውነት መሆኑን የሚጠረጥር ሰው ቢኖር የሚከተለው ነገር ጆሮ ቢሰጥ ይረዳዋል፡፡

20ከሶስት ዓመት በፊት ንጉሡ ታመው ያገራችን መኳንንት ሁሉ ወደ አዲስ አበባ ተጠሩ፡፡ ያገራችን መኳንንት ወደ ጌታቸው ሲጠሩ አሥር ወይም ሀያ ራሳቸው መሄድ ነውራቸው ነው፡፡ ስለዚህ ያንን የተሾሙበትን አገር ለመጠበቅ የሚበቃ ሠራዊት ሳይተው ወደ ጦርነት የታዘዙ ይመስል አስከትተው ይጓዛሉ፡፡ ጉዞዋቸው አንድ የኢጣልያ ሰው እንዳለው የጦር መልክ የለውም ነገር ግን ወደ ስደት የተነሣ ሕዝብ ይመስላል፡፡ ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊትም እንዴሁ ያገራችን ጌቶች ወደ ንጉሡ ከተማ በተጠሩ ጊዜ በዳር አገር ሲኖር የነበረው ያማራ ዘር ሁሉ ጨቅላን ያዘለች ሴት ሳትቀር ወደ አዲስ አበባ ተጓዙ፡፡ ጋላውም ይህንን ቢያይ ተገረመ ንጉሡ ሞቱ ብሎም አወራ በየሥፍራውም ሊሸፍት ከጀለ በእግዚአብሔር ቸርነት ሳይሆንለት ቀረ እንጅ፡፡

21እነሆ እንኳን አእምሮ ያላቸው ነገሥታት ጋላውም ቢሆን የመንግሥታችን ችሎት ነዋሪ ነው አይልም፡፡ ንጉሥ ቢሞቱ መንግሥታችን የሚሞት ይመስለዋል፡፡ እውነትም ነው ትምህርት በሌለው ሕዝብ ዘንድ ንጉሥ ማለትና መንግሥት ማለት ትርጉሙ አንድ ነው፡፡ ንጉሣቸውም የፈቀደውን ያደርጋል በመላው ህዝቡ ባሮቹ ናቸው፡፡ ጌታቸው እንደ ሞተባቸው ባሮችም ንጉሥ በሞተ ቁጥር እኔ ልብለጥ እኔ ልብለጥ ሲሉ ይጣላሉ ቶሎ ብሎም አንድ የሚቤተይባቸው ሰው ያልወጣ እንደሆነ እርስ በርሳቸው ይፋጃሉ፡፡ ደግሞም ባርያ ለጌታው ልጅ በግድ ካልሆነ በቀር ወዶ እንደማይገዛ እንዲሁም አእምሮ የሌለው ሕዝብ የንጉሡን ልጅ ብሎ አያቅፍም፡፡ አእምሮ ባላቸው ህዝቦች ዘንድ ግን መንግሥት ማለት ማሕበር ማለት ነው ንጉሣቸውም የማሕበራቸው አለቃ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ንጉሡ የፈቀደውን ያደርግ ዘንድ አይችልም ሥልጣኑ የሕዝቡ ማሕበር በደነገገው ሕግና ወግ የተወሰነ ነው፡፡ የማሕበር አለቃ ሲሞት ማሕበር እንደማይደፈርስ እንዲሁ ንጉሣቸው ቢሞት አእምሮ ያላቸው ሕዝቦች ግድ የላቸውም፡፡ ንጉሥ ቢሞት ያ በሥርዓት የሚገባው ወራሽ ይተካል፡፡ ንጉሥ ሙትዋል ዕድሜ ለንጉሥ ነው ከነምሳሌው፡፡ በጎንደር አጤዎችም ቢሆን ንጉሥ በሞተና በነገሠ ቁጥር እንዴህ ሲታወጅ ነበረ ‹‹የሞትንም እኛ ያለንም እኛ በያለህበት እርጋ፡፡››

22አእምሮ የሌለው ሕዝብ ሥራት የለውም፡፡ ሥራትም የሌለው ሕዝብ የደለደለ ኃይል የለውም፡፡ የኃይል ምንጭ ሥርዓት ነው እንጅ የሠራዊት ብዛት አይደለም፡፡ ሥራት ከሌለው ሰፊ መንግስት ይልቅ በሕግ የምትኖር ትንሽ ከተማ ሞያ ትሠራለች ስለዚህ ጋላው አጤ ምኒልክን ቢፈራ መንግሥታችንን ግን ቢንቅ እውነቱን ነው፡፡ መንግሥታችን ይህንን ፳፫ ዓመት ሙሉ የታፈረች በምኒልክ ግንባር ነው እንጅ በሥርዓታችን ደልዳልነት አይደለምና፡፡

23እንግዴህ ይህንን ካወቅን ዘንድ የትግሮችን ወግ እንመርምር፡፡ ትግሬ በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ፈጽሞ ጠፍተዋል፡፡ የትም የትም ብትሔድ በዚያች አገር የለማ መንደር አታገኝም፡፡ ሰው ከሚኖርባቸውም ጎጆዎቿ ይልቅ የድሮ ልማትዋን የሚመሰክሩ ፍራሾችዋ ይበዛሉ፡፡ የትግሬም ጎበዝ በዛሬ ዘመን ባባቱ አገር አይገኝም አውራ እንደሌለው ንብ ድርሻው ሳይታወቅ ወደ አራቱ የዓለም መዓዘኖች ተዘርተዋል እንጅ፡፡ ባገሩም ላይ ድህነት ሰፍታለች የሌሎች ወገኖች መተረብያ እስክትሆን ድረስ፡፡ ሁሉም መሬት በሰላም ሲኖር ምስኪኒቱ ትግሬ ግን ሽፍታና ወንበዴ አልተለያትም፡፡ ባባቶቹም ዘወትር እርስ በርሳቸው ሲዋጉ ይኖራሉ፡፡ ምስኪኑም የትግሬ ባላገር አጤ ምኒልክ ያጣልዋቸው እየመሰለው በሸዋው ንጉሥ ላይ ብዙ ይፈርዳል፡፡ አጤ ምኒልክን የሚያውቅ ሰው ግን ይህንን ሐሜት ሲሰማ ይስቃል፡፡ የቸሩ ምኒልክን ባሕሪ የያዘ ሰው ያፋቅራል እንጅ አያጣላም፡፡ ሰውንም ፈጽሞ ሊጎዳ አይችልም፡፡ የማያውቃቸው ሰው ግን በብዙ ክፉ ነገር ያማቸዋል፡፡ አሁን ድንገት አንድ መኮንን ታሞ በሸዋ መሬት ቢሞት እግዚአብሔር ገደለው አይባልም ነገር ግን ያጤ ምኒልክ መድኃኒት፡፡ የደንቆሮ ሕዝብ ንጉሥ መሆኑን ያንድ ወገን ጥቅሙ ብዙ ሳለ ሐሜት ያመጣል፡፡ ሌላስ ይቅርና ሰማይ ዝናብን ባይሰጥ እርሻም ብዙ አላፈራም ቢል ትምህርት የሌለው ሕዝብ በንጉሡ ያመካኛል፡፡ እንዲሁም ትግሬ ባጤ ሚኒልክ ተጎዳ ቢባል ሀሰት ነው እርስ በርሱ መስማማት ስላጣ ተበላሸ እንጅ፡፡ ትግሬን የሚያህል ትልቅ ያርበኞች ነገር እርስ በርሱ ከተስማማ ዘንድ ሊጎዱት አይቻልም፡፡ አጤ ምኒልክ ግን ባንዲት ነገር ሊታሙ የተገባ ነው፡፡ የትግሬን ሕዝብ እንደ ሕዝባቸው አልቆጠሩትም፡፡ በትግሬ መሬት ሸፍቶ ባላገሮችን ሲያጠፋ የነበረው ወንበዴ ሁሉ ሲገባላቸው ምረው ሲሾሙት ሲሸልሙት ነበሩ፡፡ ይህም በደል በወራሻቸው እንዳይደገም ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እውነትም በትግሬ ነገድ ልማትና ጉዳት ምን ቸገረኝ የሚል ንጉሥ ለራሱ ይጎዳል፡፡ ትግሬን የሚያህል ትልቅ ነገድ ቢጠፋ ለኢትዮጵያ ታላቅ ጉዳት ነው ቢለማና ቢመቸው ግን ታላቅ ጥቅም፡፡ የኢትዮጵያ መሠረት ትግሬ ነው፡፡ ከቀሩትም የኢትዮጵያ ነገዶች ይልቅ የኢትዮጵያን መንግሥት ዕድሜ ሊመኝ የሚገባው ትግሬ ነው፡፡ ይህ ግን ከብልሁ ደጃች ገብረ ሥላሴ በቀር በሌሎች የትግሬ መኳንንት ዘንድ አልታወቀም፡፡ እኒያ ጠንካራ የሃይሌ ልጅ ግን እንደነተድላ ዋህድ እንደነአሉላ አባ ነጋ ዱሮ ዘመን በጎራዴያቸው እንዳደረጉ እርሳቸውም ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ሁነው በምክራቸው የትግሬ ሰው የኢትዮጵያ መንግሥት ዕድሜ እንዲመኝ መሰከሩ፡፡ የሚበዛውም የትግሬ ሰው እንደርሳቸው ያስባል፡፡

24እንግዴህ ከጸሐፊው ልብ ውስጥ ፍርሀት ተነሣ የሰዎቹን ሀሳብ ሊመረምር ነውና፡፡ ዘመናይ ሁሉ ሊያመሰግኑት እንጅ ሊወቅሱት አይወድም፡፡ ስለዚህ ብዙ የሸዋ ሰው ሳይቆጣ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ሰውን ፈርቶ እውነቱን የሚሸሽግ ሰው እንደ ወንድ ይቆጠራልን? መንግሥቱንም የሚወድ ሰው ያ ቅዱስ ቅዱስ የሚለው አይደለም ጥፋቱን ይገልጽለታል እንጂ፡፡

25እንግዴህ ወደ ምርመራችን እንመለስ፡፡ አጤ ምኒልክ በእውነት የሸዋ ሰውና አቶ አፈ ወርቅ እንደሚሉት አዲስ ሕግጋት አውጥተዋልን? ትምህርትንስ ገልጸዋልን? እውነት አይደለም፡፡ ይህማ ቢሆን ይህን ያህል ጊዜ በሰላም እንጀራቸውን አይበሉም ነበር፡፡ ትግሬው አለቃ ተወልደ መድህን እንደሚሉት ‹‹መብራት ሳይነድ አያበራም››፡፡ ስለዚህ የዓለምን ታሪክ ብንመለከት አዲስ ሥርዓት የሚያወጣ ንጉሥ ሁሉ በህይወቱ ሳለ መከራ አይለየውም ሕዝቡ እንደ አውራ ደመኛው ያየዋልና፡፡ ደግነቱም የሚታወቅ ብዙ ዓመታት ከሞተ በኋላ ነው፡፡ የአዳምን ዘር ባህሪ በጠቅላላው ብንመለከት አዲስን ነገር የሚወድ ወገን አናገኝም፡፡ ካባቶቹ የቆየውን ካልሆነ በቀር ይልቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ያባቶቹን ልማድ ሲለውጡበት ዝም ብሎ ባልተቀበለም ጢስ እንደገባበት ንብ በተሸበረ በተናወጠም ነበር እንጅ፡፡ ወዮለት ለዚያው ንጉሥ የዛሬውን ከደማችን ጋራ የተዋሀደውን የድንቁርና ሥርዓታችንን ሊለውጥ ለሚነሣው፡፡ ለኋላ ስም ያገኛል እንጅ በሥጋው አይጠቀምም፡፡

26ይህም ነገር ባጤ ቴዎድሮስ ታሪክ ይመሰክርልናል፡፡ ያ ቋረኛ ንጉሥ ተበጣጥሰው የነበሩትን ያበሻን መንግሥት ክፍሎች በሰላው ጎራዴው ቀጥቅጦ አዋደደ፡፡ ሕዝቡንም ከካህናትና ከሹሞች ቀምበር አርነት ሊያወጣ አገር በጄ ብሎ አወጀ ትምህርትንም ሊከፍት ተከራከረ፡፡ አንባቢ ሆይ በዚህ ጥረቱ ምን ተጠቀመ ይመስልሃል? በመላው ሕዝብ በካህናትና በሹሞች ተመክሮ ተነሣበት አሳበደውም፡፡ በመጨረሻም ለባዕድ አሳልፎ ሰጠው በገዛ እጁም ሞተ፡፡ አእምሮ የሌለው ሕዝብና ልጅ ጠቃሚውን አይወድም፡፡ የቴዎድሮስ አሳብ ግን አልተፈጸመም እንጅ አልሞተም፡፡ አባ ታጠቅ ለራሱ ቢከፋው የማይረሳውን ስም ተክሎ ሞተ፡፡ እውነት ነው የመነኮሳት ኃይል ገና አላላችም ሹሞቹም ብርቱ ተቆጣጣሪ ገና አልወጣላቸውም፡፡ እስካሁንም ድረስ የተሸሙበትን አገር በገንዘባቸው እንደ ገዙት ርስት ያዩታል፡፡ ከኡ በሚወጣውም ግብር የታያቸውን ያደርጋሉ በታቻቸውም ያለ ሹምና አሽከር ከነሱ በቀር ሌላ ጌታ አያውቅም፡፡ አጣም አገኘም ከቸርነታቸው ነውና፡፡ የሆነ ሁኖ የዛሬ ሹማምንት እንደ ዱሮቹ አይደሉም መንግሥት በላያቸው እንዳለ ጥቂት ይታወቃቸው ጀምረዋልና፡፡ ኢያደረም አጥብቆ ሳይታወቃቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ የቴዎድሮስ መንፈስ አልሞተም ኢያደረ ሕይወት ይጨምራል እንጅ፡፡

27የሸዋው ንጉሥ ግን ለሕዝባቸው ያባቱን ልማድ መረቁለት፡ አዲስ ነገር እንዲቀበልላቸውም አልተከራከሩትም፡፡ ወንበዴውም ሁሉ እንዲያርፍላቸው ስለ ሥርዓት የሚበቀል ጎራዴ አልመዘዙበትም ነገር ግን በቸርነታዊ እጃቸው ወዳደባባያቸው ስበው ደጅ አስጠኑት ሹሞቻቸው ግብር ብለው ከሚያመጡላቸው ጥቂት ሲሳይም መገቡት፡፡ በራሱ ላይ ቆብን ጭኖ ወይም ትልቅን ሻሽ ጠምጥሞ ወይም መቁጠሪያ ይዞ ወደ አዲስ አበባ ቤተ መንግሥት ሊለምን የሄደም ሰው ሁሉ ባዶ እጁን አይመለስም ነበረ፡፡ ስለዚህም ትልቁም ትንሹም ምኒልክ ቸሩ ምኒልክ ይል ገባ ይላልም፡፡ ስለዚህም ጎጃሞች እንደ ሚሉት አጤ ምኒልክ በቸርነታቸው ገዙ ቢባል ውሸት አይደለም፡፡ ይህ ማለፍያ ነው ያስመሰግናልም ግን ትምህርትን ገለጹ አያሰኝም፡፡

28አንድ ልበ ብሩህ ያበሻ ሰው መሬት ትዞራለች ብሎ ቢያስተምር አሁን በቅርቡ በሀረርጌ በዳኛ ተይዞ አልነበረምን? አሁን ፲፱፻ ዓመታት ከክርስቶስ ልደት በኋላ አልፈው ሀያኛውን መቶ ዓመት ስንጀምር አንድ ሰው የተዋህዶን ሃይማኖት ቢነቅፍ ካዲስ አበባ ገበያ ላይ በደንጊያ አልተቀጠቀጠምን? እስከ ዛሬ ድረስሳ ወደ ሩቅ አገር ተሰደው ወይም ወደ አበሻችን ከሚመጡት ፈረንጆች ጥቂት ጥበብ ተምረው ያገራቸውን መንግሥት ሊጠቅሙ የሚፈልጉ ወንድሞቻችን ፕሮቴስታንት ካቶሊክም መናፍቃን የሌላ መንግሥትም ሰላዮች እየተባሉ ሲራቡ ሲከሰሱም እናይ የለምን? የነዚያን መከረኞች ስም ስንት ብለን እንቁጠር፡፡ የሚከተሉት የሁለት ሰዎች ስም ግን እንዲወርሱ የግድ ነው፡፡ እነሱም ከንቲባ ገብሩና አለቃ ታየ ናቸው፡፡ ሶስት ዓመት ምሉ አዲስ አበባ ላይ ስቀመጥ እንደ እነዚህ ሁለት ሰዎች አርጎ መንግሥቱን የሚወድ ሰው አላየሁም፡፡ ይህ ደግነታቸው ግን እስከ ዛሬ ድረስ አልታወቀላቸውም ይመስለኛል፡፡ እጅግ ያሳዝናል፡፡ የነሱን ዕድል ያየ ሰው የኢትዮጵያ መንግሥት ለወዳጅ አይጠቅምም ብሎ ተስፋ ይቆርጣልና፡፡

29ጃፓን የሚሉት መንግሥትስ እንኳን ተምሮ የመጣለትን ሊያበርር ወደ ኤሮጳ ሒዶ የሚማርለትን ሲያገኝ በገንዘብ ያግዘው ነበር፡፡ የትምሕርትን ቤት እከፍታለሁ ብሎ የሚወጣውንም የኤሮጳን ሰው እንኳን ሊከለክል በገንዘቡ እንዲመጣለት ያዋውለው ነበር፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ዓይኑን ከፈተ ሀብታምም ሆነ፡፡ በረታም ታፈረም፡፡ ቻይናና እስያም የሚባሉ ሁለት መንግሥታትም የጃፓንን መንገድ በብዙ ትጋት መከተል ጀምረዋል፡፡

30አጤ ምኒልክም እንደርሱ ያለውን መንገድ መከተል ይገባቸው ነበር አልተከተሉም እንጅ፡፡ የሸዋ ሰው ሆይ እንግዲህ አጤ ምኒልክ የገለጹት ትምህርት የት አለ ለራሳቸው አስተማሪ የሚፈልጉ ግብጦት ከሚያስተምሩባቸው ሁለት የትምህርት ቤቶች በቀርሳ የሚረባውን ሌላ የትምህርት ቤት እስቲ አሳየኝ? የታወጀውን አዲስ የመሠረት ሥርዓት እስቲ አሰማኝ? የሸዋ ሰው ሆይ ስለምን ዝም ትላለህ? ወድያው ተረታህን? አጤ ምኒልክ ሕዝባቸው እንዲማርላቸው ይመኙ ነበሩ ብትል ግን እውነትህ ነው፡፡ ለራሴ ይመቸኝ እንጅ በኋላዬ በሚሆነው ነገር ምን ቸገረኝ ይሉ ያስቡም እንዳልነበሩም አስተዋይ ሁሉ ያምንላቸዋል፡፡ ስለ ሕዝባቸው ደህንነትና ብርታት የሚበጀውን ብዙ ነገር ሲያስቡ እንደነበሩም ውልውል የለውም፡፡ ይልቁንም ሊታመሙ አቅራቢያ ብዙ ትልልቅ ነገር ጀመሩ ሊፈጽሙትም ቆርጠው ነበረ ነገር ግን ሁሉም በውጥን ቀረ፡፡ ምስኪን ኢትዮጵያ ሆይ የዕድልሽ ቀን መቸ ይነጋ ይሆን? አጤ ምኒልክ ይህን ያህል ጊዜ በጤና ሲኖሩ ኑረው በብርታት ሊጥሩልሽ ሲነሡ በበሽታ ተያዙ፡፡ ይህም ያጤ ምኒልክ ነገር እጅግ ይገርማል ሀያ ዓመት ምሉ ዝም ማለታቸው በሽታ ወይም ሞት ያመጣብኛል አይሉም ኑረው ይሆን? ምኒልክን የሚያህል ሰው በእንዲህ ያለ ድንቁርና አይታማም፡፡ እውነቱስ ይህ ነው፡፡ አጤ ምኒልክ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኤሮጳ ነገር ፈጽሞ ሳይገለጽላቸው ቀርቶ ነበረ፡፡ ሕዝባቸውም የኤሮጳን አእምሮ ያላቀፈ እንደሆነ ጠፊ መሆኑን አልተረዱትም ነበር፡፡ በዚህም ነገር ሊነቀፉ አይገባም፡፡ ማን ቢያስተምራቸው ማንስ ይህንን ነገር ቢገልጽላቸው ሳይገባቸው ቀረ? ባንድ ወገን ትምህርትን የማይወድ ሕዝብ አጠራቸው ባንድ ወገንም ሲያምኑዋቸው በነበሩ ፈረንጆች ብዙ ተታለሉ፡፡ ስለዚህ አማካሪ የሚሆናቸውን የኤሮጳን ሰው እንዳያስመጡ ሰጉ፡፡ ኋላ ኋላ ግን ወደ ግዛታቸው የሚመጡት ፈረንጆች ቢበዙ ጨዋውንና ክፉውን ለዩ፡፡ ሹማምንቶቻቸውም ይልቁንም ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስና ነጋድራስ ይገዙ የባሕር ማዶን ሥርዓት በትጋት ኢየጠያየቁ ጌታቸውን መንግሥትን በሚጠቅም ምክር ያግዙ ጀመሩ፡፡ ንጉሡም በጊዜ ብዛት ነገሩ ገባቸው፡፡ ብሩሁ ልቦናቸውም ብዙውን ትልልቅ ነገር ሊፈጽም በብዙ ብርታት ተነሣ ጀመረም የድንገት በሽታ ግን ብርታቱን አደከመበት፡፡ መድከማቸውንም አይቶ ደኃው በየጎጆው አለቀሰ፡ ያለቅሳልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ በንድያው እንኳ ይህን ያህል ያለቀስህ ምኒልክ አስቦልህ የነበረው ልማት ተገልጾልህ ቢሆን ምን ትል ኑረሃልን?

31ደግሞም አንድ ነገር እንጠይቅ፡፡ ንጉሡ ቢታመሙ አሳባቸው ስለምን በውጥን ቀረ የሚፈጽመው ሰው ታጣን? አዎን፡፡ የሚበዙቱ ሹማምቶቻቸው እንኳን የታሰበውን ነገር ሊፈጽሙ የተፈጸመውም ቢፈርስ ግድ የላቸወም፡፡ የሹሞቹም ስንፍና አያስደንቅም ካለመማራቸው የተነሣ ነውና፡፡ ያልተማረ ሰው ሁሉ የራሱን እንጂ ያገሩንና የመንግሥቱን ጥቅም ሊያስብ አይችልም፡፡ ስለዚህም በገንዘብ ይታለላል ቢኮረፍም ይሸፍታል ስለ መንግሥቱም ልማት መከራን ችሎ ተዋርዶ ከሚኖር ብዙ ሰውን ፈጅቶ አገርንም አጥፍቶ ቢሞት ወይም ቢታሠር ስም ይመስለዋል፡፡ ስለዚህ የሹሞቹ ቸልታ ፈጽሞ ይገባል፡፡

32ፈጽሞ የማይገባስ የእቴጌ ጸሐይቱ ነገር ነው፡፡ እኒያ ክብርት ሴት አገራቸውንና ሕዝባቸውን ሲወዱ እንደነበሩ ማን ይጠረጥራል፡፡ ለኢትዮጵያም መንግሥት ብዙ እንዳገለገሉ ማን አሉ ይላል፡ ባጤ ምኒልክ ጊዜ አገራችን የረጋች ሰሜነኞችና በጌ ምድሮች እንደሚሉት በጣይቱ ብጡል ብርታት ነው፡፡ እውነታቸውንም ነው፡፡ ምክንያቱ እነሱ ከሚፈክሩት ሌላ ሆነ እንጂ፡፡ እቴጌ ጣይቱ የሸዋን ቤተ መንግሥት እልፍኝ ባይዙ የሸዋ ወንድሞቻችን እናጠቃለን ሲሉ የሰሜን ኢትዮጵያውያንም አንጠቃም ሲሉ ባገራችን ላይ ሰላም አይሰፍንም ነበር፡፡ በሸዎች አሳብ ከዱሮ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ጎንደሬ ወይም ትግሬ ማለትና ክፉ ሰው ማለት ትርጉሙ አንድ ነው፡፡ ለክፉ ህዝብ በሚገባውም በባርነት አገዛዝ ሊገዙዋቸው ባልጠሉም ነበር፡፡ እቴጌ ጣይቱ ግን ለሰሜን ወገን ሁሉ ጋሻ ሁነው አገድዋቸው፡፡ እውነት ነው እስከ ዛሬ ድረስ ትልቅ የሆነ የቤተ መንግሥት ሹመት ሁሉ ይልቁንም የምኒስትርነት ሥራ በሸዎች እጅ ብቻ ነው፡፡ የትግሬ የሰሜን የበጌምድር የላስታ የጎጃም ልጅ የሆነም ሁሉ እንደ የውጭ ሰው ኢየተቆጠረ ከትልቅ የመንግሥት ምክር አይገባም፡፡ ትምህርት ስለሌለው ግን የሰሜን ሰው የዚህን ነገር ውርደት ገና አያስተውልም፡፡ በዚህ ምክንያት በሌላ ነገር ስላልተዋረደ ለጥ ብሎ ተገዛ፡፡ የእቴጌ ጣይቱም አገልግሎት ይህ ብቻ አይደለም፡ ነገር ግን ስንቱን ብለን እንቁጠረው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በመሬት ላይ እስታለ ድረስ የጣይቱ ብጡል ስም አይረሳም፡፡ ስለዚህ የበኋላው ስሕተታቸው ያሳዝናል፡፡ የዳግማዊ ምኒልክን ፈቃድ ወራሻቸው የወሎው ባላባት የልጃቸው የወይዘሮ ሸዋ ረጋ ልጅ ኢያሱ ሚካኤል ይሁን የሚለውን አላስፈጽምም ብለው ተነሥተው ነበሩና፡፡ ስለዚህም ብዙዎች መኳንንት መጀመሪያ በጀርመኑ ዶክተር ጽንትግራፍና ባስተርጓሚው በኋላ ግን በደጃች ገብረ ሥላሴና በነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ ተመክረው ተነሡባቸው ከቤተ መንግሥት ጉዳይ እንዲከለከሉም የግድ አሉዋቸው፡፡ የሚጠረጠሩ ዘመዶቻቸውም ሁሉ ታሠሩ፡፡ ይህም ሁሉ ሲሆን የወንድማቸው ልጅ ደጃች አመዴ ሲያዙ በቀር ደም አልፈሰሰም፡፡ ይህም አንድ ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው፡፡ አጤ ምኒልክ ሲደክሙ በኢትዮጵያ ብዙ ደም ይፈሳል ተብሎ በጠላቶቻቸው ተስፋ ሲደረግ ኑረዋልና፡፡ እውነትም የሸዋ መኳንንት መስማማት በማጣታቸው የመንግሥታችን ጠላቶች ተስፋ ሊፈጸም ጥቂት ቀርቶ ነበረ፡፡ እግዚአብሔር ግን እንደ ዘወትር ቸርነቱ ዛሬም ብርቱ ጋሻ ሆኖ መንግሥታችንን ከጥፋት አዳነ፡፡

33የኛ የኢትዮጵያውያን ያለፈው ታሪክ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ፍጹም የሆነ ሰላም አግኝተን አናውቅምና፡፡ የተወደደች አገራችን ዘወትር በጠላቶች ተከባ ስትኖር ነበረች ትኖራለችም፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት የውጭ ጠላት ከዚህ በፊት አላዋረደንም፡፡ አንድነትም ስንሆን ምንም የሚደፍረን እንደሌለስ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ዘወትርም በስምምና በፍቅር አድረን ብንሆን እስከ ዛሬ ድረስ ብዙውን ትልልቅ ነገር መፈጸም እንችል እንደ ነበር ጥርጥር የለውም፡፡ እግዚአብሔር ብዙ በረከት ሰጥቶናልና፡፡ ትምህርትን በቶሎ መቀበል የሚችል ልቦናና የጦረኛን ባሕሪ ማለፍያና ሀብታም አገርንም፡፡ ካለመስማማታችን የተነሣ ግን ሌሎች ሕዝቦች በአእምሮና በጥበብ እየበረቱ ሲሄዱ እኛ ወደ ኋላ ቀረን እንደ አርመኖች እስኪቆጥሩን ድረስ፡፡ የዱሮውም ያሁኑም ኑሮዋችን እጅግ ያሳዝናል፡፡ በመላው ዓለም ላይ ሰላም ሲሰፋ አእምሮ ስትበራ እኛ በጨለማ እንኖራለን እርስ በርሳችን መጠራጠርንም አልተውንም ሕዝቦቹም ሁሉ እርስ በርሳቸው በፍቅር ተቃቅፈው ስለ ልማታቸው በአንድነት ሁነው ሲደክሙ እኛ አንድ ዘርና ወንድማማች መሆናችንን ገና አልተገለጸልንም፡፡ እርስ በርሳችን መፋጀትም እስከ ዛሬ ድረስ ጅግንነት ይመስለናል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ለብርታት የሚሆነውን ስጦታ ሁሉ ሰጥቶን ሳለ ባለቤቶቹ ሰነፍን፡፡ ሌሎቹም ነገሥታት እንደ ሰነፎች ይቆጥሩናል ይንቁናልም፡፡

34የሰውም ክብረቱ ስራና አእምሮ መሆኑን ገና አላወቅንም፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ የሚያውቀውን ወንድማችን አስማተኛ ደብተራ የጅ ሥራ የሚያውቀውንም ቡዳ ፋቂም ሸማኔም እያልን እናዋርደዋለን፡፡ መንግሥታችንም አንድ ጥበብ ከሚያውቀው ዜጋው ይልቅ ያነን የማያውቀውን ያከብራል፡፡ አሁን በቅርብም ጽሕፈት የማያውቀው መሐይምን ሁሉ ባዋጅ ሹመት ያልተከለከተ እንደሆነ መንግሥታችን ከቶ አይቀናም፡፡ ባገራችን እስከ ዛሬ ድረስ ሠርተው ደክመው መብላት ነውር ነው፡፡ ለጨዋ ልጅም አይገባም ይባላል፡፡ ወታደር ተበሎ አሮጌ ጠበንጃንም ተሸክመው አንድን ሹም እንደውሻ ኢየተከተሉ ከመዋልም በቀር ሌላ ክብረት አናውቅም፡፡ ያገራችንም ሰው ሁሉ ወታደር ነኝ ባይ ነው፡፡ አንካሳውም ዕውሩም ቆማጣውም በምርኩዝ የሚሄደው ሽማግሌውም አፍንጫውን ያልጠረገ ልጅም ወታደር ነኝ ይላል፡፡ ሌላስ ይቅርና ብዙ ሴቶችም ወታደሮች ናቸው፡፡ የሚበዛው ያገራችን ሰው በወታደር ስም ይጠራል ባደባባይም ስራ ፈትቶ ሲክበሰበስ ይውላል መከረኛው ባላገር በደከመበትም እህል ይመገባል፡፡ አእምሮ ባላቸው ነገሥታት ሁሉ ሥራት ወታደር ማለት በባላገሩና በገባሩ ላይ ክፋት እንዳይመጣ የሚጠብቅ ማለት ነው፡፡ ባገራችን ግን የባላገር ደመኛ ብለን ብንተረጉመው ልክ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ማለፍያይቱ መሬታችን የሚያርሳት አጥታ ጠፍ ሁናለች ስለዚህም ደኸየን፡፡ ባደባባይ ስራ ፈትተው ከሚኖሩት ሰዎች ግን ብዙዎች አርሰው ሊበሉ ባልጠሉም ነበር የሚወድቅባቸውን ዕዳ እየፈሩ ነው እንጅ፡፡ መሬትን ቆፍሮ ሊበላ የሚሻ ሰው ባገራችን መከራው ብዙ ነው፡፡ ገና ማረሻውን በመሬት ሳይተክል ግብር አምጣ የሚለው ሹም ይመጣል፡፡ ሲደክም ውሎም ወደ ቤቱ ሲመለስ ምሽቱን ወታደሮች ጋግሪ ወጥ ሥሪ እያሉ ሲያዳፍዋት ያገኛታል፡፡ ገዦቹም ባዘዙት ቁጥር የቤቱን ጥሎ ቤታቸውን እንደ ባርያ ደሞዝ አልባ ሲሠራ ይውላል፡፡ በያመቱም የሚከፈለውም ዕዳ አያውቅምና ሥጋት አይለየውም፡፡ አእምሮ ባላቸው ሕዝቦች ዘንድ ግን እርሻን የሚጀምር ሰው እስኪደረጅ ድረስ ሁለት ወይም ሶስት ዓመት ምሉ በግብር አይነካም፡፡ ከዚህም በኋላ በያመቱ የሚከፍለው ግብር በሥራት የተለየ ነው ስለዚህም አይከብደውም፡፡ ወታደርና ሹምም ወደ ቤቱ ደጃፍ አይደርስም፡፡ ያለመንግሥት በያመቱ ሊከፍለው ከተደነገገውም ግብር በቀር ደክሞ የሚያገኘው ነገር ሁሉ ገንዘቡ እንደሆነ ያውቃልና ተግቶ ይሠራል፡፡ ተግቶም የሚሠራ ሰው ሁሉ ካልተቀማ በቀር ሀብታም ይሆናል፡፡ ሕዝቡም ሀብታም የሆነ መንግሥት ብርቱ ነው፡፡ ሕዝቡ የደኸየ እንደሆነ ግን ደካማ፡፡ እኛ ግን ሥርዓት የለንም ስለዚህም ሰነፍን፡፡ በመሬታችን ውስጥ የተሸሸገውም ሀብት ፈላጊ አጣ ስለዚህም ደኸየን፡፡

35ጥጥን የሚያፈራና በግን ለማርባት የሚሆነው መሬታችን ሥራ ሲፈታ ከውጭ አገር የመጣውን የማይረባውን ጨርቅ እንለብሳለን፡፡ ከመሬታችንም ውስጥ ብረትና ከሰል ሲገኝ መሣርያችንን ሁሉ ከባሕር ማዶ እናስመጣለን፡፡ ሌላስ ይቅርና አንድ ብልህ የትግሬ ሰው እንዳለው መርፌንም ቢሆን ሠርተን አንችልም፡፡ የሀብታምም መሬት ጌቶች ሳለን እንራባለን፡፡ ይህም ድህነትና ችጋር የስንፍናችን ፍሬ ነው፡፡

36በፊትህ ወዝ እንጀራ ትበላለህ ወደ ተፈጠርህባት ምድር እስክትመለስ ድረስ (ዘፍጥረት ፫፡፲፱) እግዚአብሔር ምድርን ፈጠረ፡፡ ለሠራተኛው ለብልሁ ሰውም በረከት ለሰነፉም አይደል፡፡ ስለዚህም እነዚያ ሥራንና ትምህርትን የሚወዱ ሕዝቦች ውለው አድረው በሰነፎቹ ሕዝቦች ላይ እንዲጌተዩ የማይነቀነቅ ዘላለማዊ ሥርዓት ነው፡፡

37ምነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከንቅልፍህ መቸ ትነሣለህ? በዓለም ላይ የሚደረገውን ነገር ለማየትስ ዓይንህን መቼ ትከፍታለህ፡፡

38ከላይ እንዳልነው እግዚአብሔር አምና መንግሥታችንን አዳነልን፡፡ ስለሆነ ይገባናል እናውቅ ዘንድ መንግሥት ያለው ሕዝብ ነው መባል ብቻ ጥቅምና ክብረት እንዳይሆን፡፡ እጀጠባብና ሱሬ አልባ ካባ ላንቃ ያልለበሰ ሰው መኮነን እንደማይሆን ባለመንግሥት ከሆኑ ዘንድ እውነተኛ አእምሮ ያለው ባለ መንግሥት ሕዝብ መሆን ያስፈልጋል፡፡

39በዙሪያችን ያሉትን አገሮች ብንመለከት አእምሮ ያላቸው ሕዝቦች በብዙ ትጋት ሲያለምዋቸው እናያለን፡፡ ይልቁንም በደርቡሾች ጠፍቶ የነበረውን የሱዳንን መሬት ብናይ እንግሊዞችን የሚመስል የአእምሮ ሕዝብ ሊገዛው ምድረ በዳም ቢሆን የደስታ ገነት እንዲሆንም ይመሰክርልናል፡፡ በዙርያችን ቅኞችን ኮሎንዮች ይዘው ያሉ ሕዝቦችም የአምሮዋቸው ኃይል እንቅፋት ሁሉ እያሸነፈ ወደ ፊት ይገፋል መሬት ጠቦታልና፡፡ አእምሮም በአእምሮ ካልሆነ በቀር በሌላ አትታገድም፡፡ ስለዚህ ወዮለት በድንቁርናው ለሚቀመጥ ሕዝብ ውሎ አድሮ ይደመሰሳልና፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከፈረንጆች ጋራ ከተዋወቅን ብዙ ጊዜ አልፏል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ አንዳች አልተማርንም፡፡ ስለዚህም መንግሥታችን እንዳትጠፋ ያሰጋል፡፡ የኢትዮጵያችን ሰው ግን ይህንን ቢነግሩት እንዲህ ሲል ይመልሳል፡፡ እግዚአብሔር አገራችንን አሳልፎ ለባእድ አይሰጣትም፡፡ የመንግሥታችንም መኳንንት ይህንን እያሉ በስንፍና ይኖራሉ፡፡ እውነትም ቸሩ እግዚአብሔር የመንግሥታችን አርነት እንዳትጠፋ ብዙ ጊዜ ከለከለ፡፡ እኛ ግን እስከ ዛሬ ለቸርነቱ የተገባ ሕዝብ መሆናችንን አላሳየንም፡፡ በዚህ ምክንያት ውሎ አድሮ እንዳይፈረድብን እንጠንቀቅ እንትጋም፡፡ መንግሥታችንም እንድትቀና የሚከተሉት አሥር ነገሮች በቶሎ ቢፈጸሙ ማለፊያ ነበር፡፡

40መጀመርያ ለመንግሥት የሚሆን ገንዘብና ለንጉሡ የሚሆነው ገንዘብ በሥርዓት ይለይ፡፡ ሹሞቹም በደሞዝ ይደሩ፡፡ ካገር በሚወጣውም ግብር ለመንግሥት ይግባ፡፡ የጦርም ሠራዊት ሁሉ የንጉሥ ይሁን፡፡ ያገር ምስለኔና የጦር አለቃ በያገሩ ይለይ፡፡ መጀመርያው ባላገሮቹን የሚያዝ ሁለተኛው ግን ወታደሮቹን፡፡

41የንጉሡና የመንግሥት ገንዘብ የተባለውም ትርጉሙ እንዲህ ነው፡፡ የንጉሥ ገንዘብ ማለት ያ ለግብርና ለሌላ የንጉሡ ቤት ጉዳይ የሚያስፈልግ ገንዘብ ነው፡፡ የመንግሥት ገንዘብ ማለት ግን ያ ለሠራዊት ደሞዝ ለመንገዶችና ለትምህርት ቤቶች ማሠርያ የጦር መሣርያዎችም መግዣ ለሌላ እንዴህ የመሰለውም የውጭ ጉዳይ የሚሆነው ገንዘብ ነው፡፡

42ሁለተኛው ሕዝቡ ለመንግሥት የሚከፍለው ግብር እንደየሀብቱ መጠን ቁርጥ ሁኖ ይታወቅለት፡፡ የሕዝቡም ቁጥር በመዝገብ ይግባ፡፡ እንዲሁም በየዓመት የሚወለደውና የሚሞተውም የሚጋባውና የሚፋታውም በመዝገብ ይታወቅ፡፡

43ሶስተኛ ሕዝቡም የሚከፍለው ግብር በብር እንጅ በእህል በማርም በፍሪዳም አይሁን፡፡ የመንግሥት ሥራ ሁሉም በባላገር አይሥራ በባለ ደሞዝ እንጅ፡፡ ባላገሩም የሚከፍለው ግብር በመላው አገር ትክክል አይሁን ያውራጃው ሀብት ኢየታየ እንጅ፡፡ አሁን በጌምድር ሰሜን ላስታ ጎጃም የጁ ወሎ ብዙ ብር አይገኝበትም ስለዚህ እንደ ሀብታሞቹ ሸዋና ትግሬ ሊገብሩ አይቻላቸውም፡፡

44አራተኛ ያማርኛ ቋንቋ ገና ሰዋሰው አልተበጀለትም፡፡ ስለዚህ መንግሥታችን ከያገሩ ሰዋሰው የሚያውቁትን ሊቃውንት ሰብስቦ ያማርኛን ቋንቋ ሰዋሰው ቢያስወጣ ደግ ነው፡፡ በያገሩ አውራ ከተማ እንደ ኤሮጳ ሥርዓት ያበሻን ፊደልና ያማርኛን ቋንቋ ማስተማርያ ቤቶች ይክፈቱ፡፡ ባዲስ አበባ በሀረርጌ በጎንደር በአክሱም ግን አውራ የትምህርት ቤቶች በንዲህ ያለ ሥርዓት ይቁሙ፡፡ በያንዳንዱ የትምህርት ቤት አራት የኤሮጳ መምሕራንና አምስት ያበሻ መምህራን ይሹሙበት፡፡ የያንዳንዱ የኤሮጳ መምህርም ሥራ ይህ ይሁን አንዱ የቁጥርና የሒሳብ አስተማሪ ሁለተኛው የዓለም ታሪክና ጀዮግራፊያ አስተማሪ ሦስተኛው የእንግሊዝ ቋንቋ አስተማሪ አራተኛው የፈረንሳዊ ቋንቋ አስተማሪ፡፡ በአክሱም ግን በእንግሊዝ ቋንቋ መምህር ፈንታ የኢጣሊያ ቋንቋ አስተማሪ ቢሾም ይሻላል፡፡ ያበሾቹ መምህራን ሥራ ግን ይህ ይሁን፡፡ አንዱ የወንጌል አስተማሪ ሁለተኛው ያማርኛን ቋንቋ አገባብ አስተማሪ ሦስተኛው የመንግሥታችንን ታሪክ አስተማሪ አምስተኛው የፍትሐ ነገሥት አስተማሪ፡፡

45ስላራቱም አውራ የትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጉን መምህራን አሥራ ስድስት የኤሮጳ ሰዎችና ሀያ አበሾች ናቸው፡፡ አንድ ደልዳላ የኤሮጳ መምሕርም በ፪ ሺህ ብር ላመት ይገኛል፡፡ ያበሻውም አንድ አስተማሪ ፫ መቶ ብር ባመት ቢያገኝ ይበቃዋል፡፡ ስለዚህ ለመምሕራን የሚሆነው ደሞዝ በየዓመቱ ፴፰ ሽህ ብር ነው፡፡ ለትምሕርት ቤቶችም ሌላ ጉዳይ ሁሉ ፻፴፪ ሽህ ብር ይበቃል፡፡ ስለዚህ ላውራዎቹ የትምህርት ቤቶች የሚያስፈልገው ኪሳራ ፻፶ ሺህ በዓመት ብቻ ነው፡፡ ፊደልን ያላጠና ልጅም በአውሮቹ የትምህርት ቤቶች አይግባ፡፡ የፊደል ማስተማርያ ቤት ግን ያውራጆቹ ገዦች እንዲያስባቸው መንግሥት የግድ ይበላቸው፡፡

46ያገራችንም ሰው ፊደልን ለመማር ቢተጋ አገራችን ቶሎ በቀናች፡፡ ፊደልንም መማር እጅግ ቀላል ነገር ነው፡፡ በሱዳን መሬት የሚኖር አንድ ትጉህ የወሎ ልጅ ዕድሜው ፴፭ ዓመት እስኪሆን ድረስ ምንም አያውቅም ኑሮ አሁን አማርኛንና አረብኛን አጥርቶ ይጽፋል፡፡ ብዞችም ያገራችን ሰዎች የዚያን ብልህ ወሎዬ መንገድ ቢከተሉ አገራችን በተጠቀመች፡፡ ደግሞም የኤሮጳን ሠራተኞች አምጥተው ባዲስ አበባ በጎንደርም እንዲሁም በአክሱም የጅ ሥራ ማስተማርያ ቤቶች ቢበጁ ማለፍያ ነበር፡፡ መንግሥትም ለንደዚህ ያሉ የትምህርት ቤቶች ምንም ብዙ ዋጋ ቢያጠፋ ግድ የለም ነበር፡፡ ወድያው የሚያስፈልገውን ሥራ በነዚያ የትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሠራ ነበርና፡፡ እንደዚህ ያለ ጠቃሚ የትምህርት ቤት በካርቱም ከተማ ተበጅተዋልና መንግሥታችን ወደዚያ ተመልካች ይላክ፡፡

47አምስተኛ ፍትሐ ነገሥታችን ከዛሬው ያደባባይ ሥርዓት ጋራ አይስማማም፡፡ ስለዚህ መንግሥት የሥርዓት አዋቆችን ሰብስቦ ከኤሮጳ ሥርዓት ጋራ ተስማማ ፍትሐ ነገሥት ያውጣ፡፡ ይህም ሲደረግ የኤሮጳን ሥርዓትን የሚያውቅ አማካሪ ያስፈልጋል፡፡ የተጻፈ ሥርዓት የሌለው መንግሥት ብዙ ዕድሜ የለውም፡፡

48ስድስተኛ ያገራችን ሠራዊት ሥርዓት የለውም ስለዚህ የኤሮጳን መኳንንት አምጥተው ሰልፍን ቢማር ማለፍያ ነበር፡፡ እንዲሁም የኤሮጳን መምሕራን አምጥተው ባዲስ አበባ ላይ የጦር ትምህርት ቤት ይበጅ፡፡ ላገራችን የሚስማማ ማለፍያ ዓይነት የጦር ትምህርት ቤትም በካርቱም ከተማ ተበጅቷል፡፡ ስለዚህ መንግሥታችን ወደዚያ ተመልካች ይስደድ፡፡ የሠራዊትም ብዛት በልክ ይሁን፡፡ ሠራዊት ቢበዛ መንግሥት ይደሄያል እንጅ አይበረታም፡፡

49ሰባተኛ የዛሬው የመንግሥታችን ብር የተበላሸ ነው፡፡ ሥርዓትና ውል የለውም፡፡ ባንዱም አውራጃ በጨው በሌላው በጥይት ይሰፈራል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለመላው ኢትዮጵያ የሚሆን የገንዘብ ሥርዓት በቶሎ ያላወጣ እንደሆነ ንግድ ሊለማ አይችልም፡፡

50ስምንተኛ ላገራችን ነጋዴ ሥርዓት እስኪወጣለት ድረስ መንግሥታችን አይቀናም፡፡ በሩና ቀራጩ ብዙ ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት አንድ ደፋር የጎንደር ነጋዴ በመተማ ግመሎች እንደተወደዱ ሰምቶ ግመሎችን ሊገዛ ወደ ጥልጣል መሬት ወረደ፡፡ ገዝቶ ሲመለስ ያገኘውንም መከራ እንዲህ ሲል አጫወተኝ ከጥልጣል መሬት ግመሎችን ይዤ ተነሥቼ መተማ እስክገባ ድረስ ካምስት በሮች ላይ ቀረጥ ከፈልሁ፡፡ በየበሩም ጉቦ እስኪቀበሉ ድረስ በረኞቹ አናሳልፍም እያሉ መከራ ሲያበሉኝ ነበሩ፡፡ መተማም ደርሼ ግመሎችን ብሸጥ ስላገኘሁት መከራ የሚክስ ጥቅም አላፈራሁም፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ ዓይነት ንግድ እነግዳለሁ ብዬ አይደግመኝም፡፡ ያ ሰው እውነቱን ነው፡፡ የግመሎቹም ንግድ ቢቀር የሚጎዳ እርሱ ብቻ አይደለም ነገር ግን ከሁሉ ይልቅ ያገራችን መንግሥት ያገራችን ቀረጥ ሥርዓት ያለው ቢሆን ብዙ ግመሎች ሲሸጡ መንግሥት ገንዘብ ያገኝ ነበር፡፡ ነጋዴዎቹም በሚያገኙት ትርፍ በሬና ላም ገዝተው ወይም በሌላ ዓይነት ሥራ አገርን ባለሙ፡፡ ግመሎቹ አርጅተው እስኪሞቱ ድረስ የጥልጣልን ሜዳ ሣር ቢበሉ ግን መንግሥታችን የሚያገኘው ጥቅም ምንድር ነው፡፡

51ባንድ መንግሥት ውስጥ ብዙ በር ሊበጅ አይገባም፡፡ ለመንግሥት ትልቅ ጉዳት ነውና፡፡ ምነው ወደ ሱዳን ወይም ወደ ሐማሴን ተመልካቾች ሰደን ሥርዓት አንማርምን?

52ዘጠነኛ ሕዝቡ ባንድ መንግሥት ውስጥ መሆኑን አጥብቆ እንዲታወቀው አገሩን የሚዞሩ ተቆጣጣሪዎች ይሹሙበት፡፡ እነሱም ባገር ግዛት ከሚኒስትር በታች ይሁኑ፡፡

53አሥረኛ የሃይማኖት አርነት ይታወጅ፡፡ የሃይማኖት አርነት ጥቅም መሆኑን የሚያውቅ ብዙ ሰው ይኖራል፡፡ ስለዚህ የሚከተለውን ብናስተውል ደግ ነው፡፡ ያገራችን ሰው ተዋህዶ ሃይማኖት ከሁሉ ሃይማኖት ይበልጣል ብሎ ያምናል፡፡ በልጦ ግን ምን ረባን? ማንስ አወቀው? ያገራችን ካህናት መንግሥት ጠበቃቸው ሁኖ ሌላ ሃይማኖታቸውን ለሕዝቡ ሊገልጹለት አሳብ የላቸውም፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ እንኳን ተዋህዶ ማለት ምንድር እንደሆነ ሊለይ የክርስቲያን ሃይማኖት አውራ መሠረት የወንጌልን ቃል አያውቅም፡፡ ስለዚህ አጉል ቀረ የሃይማኖት አርነት እስኪታወጅ ድረስም አጓጉል ይቀራል፡፡ ለዚህም ነገር ምስክር በሀማሴን እናገኛለን፡፡ በዱሮ ዘመን በዚያች አገር መሐይምንስ ይቅርና ብዙ ቄሶች ሃይማኖታቸውን ሳያውቁ ይኖሩ ነበሩ፡፡ ፕሮተስታንቶችና ካቶሊኮች ከመጡ ወዲህ ግን ትልቁም ትንሹም የወንጌልን ቃል አውቆ በትርጉሙ ይከራከራል፡፡ ካህናትም በላምጣ ቢበዛባቸው ያስተምሩ ጀመር በዚህ ምክንያት የሃይማኖት አርነት ቢታወጅ ሃይማኖ ይታወቃል እንጅ አይጠፋም፡፡

54ደግሞም ባገራችን አንድ የድንቁርና ነገር አለ፡፡ ሃይማኖቱ ተዋህዶ ያልሆነ ሰው ሁሉ እንደ ርኩስ ይቆጠራል፡፡ ይህም እጅግ ያስቃል፡፡ አእምሮ የሌለው ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ሳያውቅ የእግዚአብሔር ጠበቃ ሊሆን ይወዳል፡፡

55ሃይማኖት የልብ ነገር ነው ስለዚህ ሰማያዊው ንጉሥ እንጅ የዚህ ዓለም ንጉሥ አይቆጣጠረው፡፡ ወንጌል የቄሣርን ለቄሣር ስጡ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ያለውን በዚሁ ቢተረጎም ለመንግሥታችን ሳይበጅ አይቀርም፡፡

56እነሆ ይህ ሁሉ ባጤ ምኒልክ ታስቦ ኑሮ ይሆናል ነገር ግን አልተፈጸመም፡፡ ስለዚህ በክቡር ወልዑል ወራሻቸው በልጅ ኢያሱ እንዲፈጸም ተስፋ እናድርግ፡፡ ክቡር ወልዑል የመንግሥት ወራሽም ይገባቸዋል ያውቁ ዘንድ ትልቅ ውርድ በራስ በላያቸው እንደተሸከሙ፡፡ የዛሬው የኢትዮጵያ ንጉሥ ሥራ እንደ የዱሮቹ አይደለም፡፡ የዚህ ዓለም ንግሥት በዱሮ ዘመን ድንቁርና ነበረች፡፡ ዛሬ ግን የማትቻል ብርቱ ጠላት ተነሣችባት እርስዋም የኤሮጳ አእምሮ ትባላለች፡፡ ለርስዋም ቤቱን የሚከፍት ክብረት ይጨምራል ቤቱን የሚዘጋባት ግን ይደመሰሳል፡፡ ኢትዮጵያችን የኤሮጳን አእምሮ የተቀበለች እንደ ሆነ የሚደፍራት ጠላት የለም፡፡ ያልተቀበለች እንደ ሆነ ግን ትፈርሳለች ወደ ባርነትም ትገባለች፡፡ በዚህ ምክንያት ክቡር ወልዑል ያጤ ምኒልክ ወራሽ የጃፓን መንግሥት እንዴት እንዳደረገ አስመርምረው መንገዱን እንዲከተሉት ተስፋ እናርግ፡፡ በጌ ምድሮች እንደሚሉት ባገራችን ርስት የተተከለ በዳግማዊ ኢያሱ ነው፡፡ ስለዚህም በክብር ወልዑል ልጅ ኢያሱ ብርታት ደግሞ የኢትዮጵያው መሬት የኢትዮጵያውያን የዘላለም ርስት እንዲሆን በብዙ እንመኛለን፡፡

Il testo e gli altri elementi (illustrazioni, file importati) possono essere utilizzati con OpenEdition Books License, se non diversamente specificato.

Questa pubblicazione digitale è stata realizzata tramite il riconoscimento ottico dei caratteri automatico (OCR).

Acquista

Cerca su OpenEdition Search

Sarai reindirizzato su OpenEdition Search